በሰጠመችው ጀልባ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 60 ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4/2010) የመን ከመድረሷ በፊት ባለፈው ሃሙስ በሰጠመችው ጀልባ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 60 መድረሱ ተገለጸ።

አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም እንዳስታወቀው በየዕለቱ በነፍስ አድን ሰራተኞች ፍለጋ ተጨማሪ አስከሬኖች እየተገኙ ነው።

100 ኢትዮጵያውያንን አሳፍራ ባለፈው ረቡዕ ከቦሳሶ የተነሳችው ጀልባ ከመዳረሻዋ የመን የወደብ ዳርቻ ከመድረሷ በፊት የመስጠም አደጋ እንደደረሰባት መዘገቡ ይታወሳል።

በወቅቱ የ46 ኢትዮጵያውያን አስከሬን መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን በነፍስ አድን ሰራተኞች ተጨማሪ 14 አስከሬኖች መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

መነሻዋን ከቦሳሶ ወደብ ፑንትላንድ ያደረገችው አነስተኛ ጀልባ ከአቅሟ በላይ ጭና ነበር።

100 ሰዎችን አሳፍራ ወደ የመን የባህር ዳርቻ እያመራች እንደነበር የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም መረጃ ያመልክታል።

ጀልባዋ ያሳፈረቻቸው በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆኑም ተገልጿል። ረቡ አመሻሽ ላይ የተነሳችው ጀልባ ሀሙስ ጠዋት ከየመን የወደብ ዳርቻ ከመድረሷ በፊት ግን የመስመጥ አደጋ እንደገጠማት መዘገቡ የሚታወስ ነው።

አይ ኦ ኤም ሀሙስ ዕለት ባወጣው ሪፖርት በነፍስ አድን ሰራተኞች አማካኝነት በህይወት ሊገኙ የቻሉት 38 ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው።

የ46ቱ ኢትዮጵያውያን አስክሬን በዕለቱ የተገኘ ሲሆን 16ቱ ግን በህይወትም በሞትም ሊገኙ እንዳልቻሉ መገለጹ የሚታወስ ነው።

እንደአይ ኦ ኤም መረጃ ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ ፍለጋው የቀጠለ ሲሆን በሶስቱ ቀናት አሰሳ ተጨማሪ 14 አስክሬኖች በመገኘታቸው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 60 ደርሷል።

2ቱ አሁንም እንዳልተገኙ ነው በአይ ኦ ኤም ዘገባ ላይ የተገለጸው። በነፍስ አድን ሰራተኞች የሚደረገው ፍለጋ ስለመቀጠሉ የተገለጽ ነገር የለም።

በአደጋው ያለቁት በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ለኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ተመዝቧል።

በየዓመቱ ከ100ሺህ ሰዎች በላይ ባህር እያቋረጡ የመንንና ወደሌሎች አረብ ሀገራት የሚሰደዱ መሆናቸው በአይ ኦ ኤም መረጃ ላይ ተመልክቷል።

ተመሳሳይ አደጋዎች በየጊዜው የሚከሰቱ መሆናቸውን የጠቀሰው አይ ኦ ኤም ችግሩ እየከፋ መምጣቱ አሳሳቢ ነው ሲልም ገልጿል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ለሁለተኛና ከዚያ በላይ የመጡ መሆናቸውን አይ ኦ ኤም ገልጾ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከሚደረጉት መሃል አብዛኞቹ ተመልሰው በዚህ አደገኛ የባህር መስመር ይሻገራሉ።