በኢትዮጵያ የገንዘብ እጥረት የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4 /2010)የገንዘብ እጥረት ቀውስ የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን  የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገለጸ።

የ2011 በጀትም 59 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳለበት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ገልጸዋል።

የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የገንዘብ እጥረት ቀውስ እንደገጠመው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገልጿል።

እጥረቱ በፍጥነት መፍትሔ ካልተገኘለት ኢኮኖሚውን በመጉዳት ማህበራዊ ችግር ሊፈጥር እንደሚችልም ነው የተገለጸው፡፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶር አብርሃም ተከስተ የ2011 ረቂቅ በጀትን ሐሙስ ግንቦት 30 / 2010 ለፓርላማ አቅርበዋል።

በተለይም ከ2008 ጀምሮ ግን የገንዘብ እጥረቱ ጎልቶ በመውጣት ወደ ኢኮኖሚ ቀውስነት የመሸጋገር አዝማሚያ እየታየበት መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

‹‹ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ደካማ በመሆኑ ለልማት የሚያስፈልጉ የካፒታል ጥሬ ዕቃዎች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሠረታዊ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ፈታኝ ሆኗል፤ ›› ሲሉም ነው  ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

በሃገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው የውጭ ምንዛሪ ደካማ ስለሆነ፣ የአገሪቱን ልማት ለማስቀጠል የውጭ ፋይናንስ በተለይም የውጭ ብድር ለማግኘት እንቅፋት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የሚኒስትሩ ንግግር የሚያስረዳው የአገሪቱ የብድር አጋር የነበሩ የውጭ መንግሥታትና ተቋማት ጭምር አዲስ ብድር ከመስጠት መቆጠብ መጀመራቸውን ነው፡፡

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዶክመንት እንደሚያስረዳው፣ መንግሥት በቀጥታ የተበደረው የውጭ ዕዳ ክምችት በዚህ ዓመት 24.75 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ በ2009 ደግሞ 13 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡

ከወጭ ንግድ ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መጠን መጨመር ይቅርና በነበረበት ማቆየት እንኳን ባለመቻሉ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ አሳሳቢ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በ2009 ታቅዶ ከነበረው የታክስ ገቢ 39 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንዳልተቻለ፣ ለዘንድሮው በጀት ዓመት ከታቀደው የታክስ ገቢ ደግሞ 50 ቢሊየን ብር እንደማይሰበሰብ ከወዲሁ መታወቁንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደ በ2011 እንዲሸጋገሩ መንግሥት መገደዱን፣ ይህ ሁኔታም በመንግሥት ላይ የበጀት ጫና መፍጠሩን ነው የገለጹት፡፡

የ2011 በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 59.3 ቢሊየን ብር በአገር ውስጥ የገንዘብ ህትመትን ጨምሮም የሚሸፈን እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከቀረበው የ2011 በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 91.7 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 113.6 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለክልል መንግሥታት የበጀት ድጋፍ 135.7 ቢሊየን ብር ሆኖ መመደቡን በሀገር ውስጥ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡