ጋዜጠኛ እና መመህርት ርዮት አለሙ የዩኒስኮ ጉሌርሞ ካኖ የፕሬስ ነጻነት አሸናፊ ሆነች

ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓም የሚከበረውን የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ዩኒስኮ በእያመቱ የሚያዘጋቸውን የዘንድሮውን ሽልማት ፣ ኢትዮጵያዊቱ የፕሬስ ጀግና ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ አሸንፋለች።

ርእዮት ከዚህ ቀደም የኢንተርናሽናል ውሜንስ ሚዲያ ፋውንዴሽን ሽልማትን አሸንፋለች።  በእስር ቤት በምታሳየው ጽናት የመላው ኢትዮጵያውያንን ቀልብ የሳበቸው ርእዮት አለሙ በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እንግልት ቢደርስባትም እስካሁን ፈተናውን በጽናት ተወጥታለች። ርእዮት በከፍተኛ ህመም ብትሰቃይም ፣መንግስት ያቀረበላትን የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ከህመሟ ጋር ችግሩን ለመጋፈጥ መወሰኑዋ ከኢትዮጵያ አልፎ አለማቀፉን ማህበረሰብ በማስደመም ለተለያዩ ሽልማቶች እንድትታጭ አድርጓታል።