ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ አብዛኞቹ የአማራ ተወላጆች ተመለሱ

ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከከማሺ ዞን በሀይል ተፈናቅለው በፍኖተሰላም ከተማ ሰፍረው የነበሩ የአማራ ተወላጆች የተለያዩ ወገኖች በመንግስት ላይ ባሳደሩት ጫና ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንደሚለሱ ቢደርግም፣ ከመተከል ዞን በተመሳሳይ መንገድ ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ ሰፍረው የነበሩት ከ2 ሺ በላይ ዜጎች አፋጣኝ መልስ አጥተው መቆየታቸውን በተደጋጋሚ ስንዘግብ ቆይተናል።

ዛሬ ከዞኑ ባገኘነው መረጃ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደሚለሱ ተደርገዋል። የመንግስት ባለስልጣናት ከ16 በላይ መኪኖችን በማቅረብ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደሚለሱ አድርገዋል።

ምንም እንኳ ተፈናቃዮች ወደ መጡበት አካባቢ እንደሚለሱ መደረጋቸውን በአወንታዊ መልኩ ቢረዱትም፣ በክልሉ በዘላቂነት እንኖራለን ብለው እንደማያስቡ ሳይገልጹ አላለፉም።

የክልሉ ባለስልጣናት ስትራቴጂ ፣ የአማራ ተወላጆች በክልሉ ምንም አይነት መሬት እንዳይገዙ በማድረግ፣ የጉልበት ስራ ለመስራት በሚቀጠሩበት ጊዜም የሚከፈላቸውን ዋጋ ዝቅ በማድረግ እና በአጠቃላይ በክልሉ ተመችቶቸው እንዳይኖሩ በማድረግ በራሳቸው ጊዜ አካባቢውን ቀስ በቀስና ድምጽ ሳያሰሙ ለቀው እንዲወጡ የማድረግ ዘዴ ለመከተል ማሰባቸውን የአነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።

ሰዎቹ እንደሚሉት በክልሉ የሚካሄደው ቅስቀሳ በተወላጅ ብሄረሰቦችና በአማራ ተወላጆች ማከከል ደም መፋሰስ እንዲኖር የሚያደርግ ነው።

የክልሉ መንግስት ለተፈናቃዮች ያተወሰደባቸውን ንብረት በመመለስ፣ የደህንነት ዋስትና በመስጠትና በክልሉ ውስጥ ለመንግስት የሃላፊነት ቦታዎች የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት እንዲሰጣቸው በማድረግ የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ካልቻለ፣ እንዲሁም የፌደራሉ መንግስት ይህን ያደረጉ ከወረዳ እስከ ፌደራል መንግስት የሚገኙ ባለስልጣናት በህግ እንዲጠየቁ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ካሳ እንዲከፈል ካላደረገ አሁን የተወሰደው እርምጃ ጊዜያዊ ማስታገሻ ተድርጎ ሊታይ ይችላል በማለት የህግ ባለሙያዎች  አስተያየታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።

መንግስት በተመሳሳይ መንገድ ከደቡብ ክልል ከጉራ ፈርዳ እና ከሚኒት ወረዳዎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እና ይቅርታ ጠይቆ ወደ ቦታቸው እንዲመልስ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች  እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ይታወቃል።