አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በኑሮ ውድነቱ መማረሩን ቀጥሎአል

ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኑሮ ውድነቱ ቅናሽ ያሳይ ይሆን በማለት ኢትዮጵያውያን ከአመት አመት ተስፋ ቢያደርጉም ተስፋቸው ግን ከተስፋነት እንዳልዘለለ በተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአምስት ክልሎች የሚኖሩ ዘጋቢዎቻችን አጠናቅረው የላኩት ዘገባ እንደሚያመለክተው በሁሉም ክልሎች የኑሮ ውድነቱ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በመላ እየጠበሰ ነው።

በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል  የኑሮ ውድነቱ ተባብሶ በመቀጠሉ ህዝቡ ኑሮውን በአግባቡ መምራት እየተሳነው ነው። በድሬዳዋ፣ ሀርር እና ሌሎችም አካባቢዎች አንድ ኩንታል ጤፍ እሰከ 2 ሺ ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ የኑሮ ውደነቱ መባባሱ ህዝቡን ተስፋ እያስቆረጠ መምጣቱን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሰዎች ይገልጻሉ።

በደቡብ ክልል በሚገኙ አብዛኛቹ ክልሎች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች እና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የኑሮ ውድነቱ በሞት እና በህይወት መካከል የጣላቸው መሆኑን ለኢሳት የደቡብ ክልል ዘጋቢ ገልጸዋል። ስኳር እና ዘይት ከገበያ መጥፋታቸውን ፣ በተለይም የእንዱስትሪ ምርቶች ዋጋቸው እየናረ መምጣቱን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ። ከማዳበሪያ ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ በእዳ እየተሰቃየ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአማራ ክልልም እንዲሁ አብዛኞቹ የመንግስት ሰራተኞች የሚያገኙት ወርሀዊ ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር እንዳላስቻለቸው ገልጸዋል።

የማእከላዊ ስታትስቲክስ መስሪያ ቤት ባወጣው የመጋቢት ወር ሪፖርት የ2005 ዓም የ12 ወራት ተንከባላይ አማካኝ አገራዊ የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በ18 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በመጋቢት ወር 2005 ዓም አገራዊ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካኝ የምግብ ዋጋ ግሽበት በ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የ12 ወራት ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች የዋጋ ግሽበትም በ17 በመቶ ጨምሯል።

በመጋቢት ወር የታየው አጣቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው የካቲት ወር 2005 ዓም ጋር ሲነጻጸር ከአንድ በመቶ ያላነሰ ጭማሪ አሳይቷል።

መንግስት በየጊዜው የሚንረውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር እንደተሳነው አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ። መንግስት የኑሮ ውድነቱ በከፊል የሚጨምረው  የህዝቡ ኑሮ እየተሻሻለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ፍጆታ በመጨመሩ ነው ይላል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በማነጋገር ተጨማሪ ዘገባ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።