ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ2012 የፔን የፅሁፍ ነፃነት አለምአቀፍ ተሸላሚ ሆነ

ሚያዚያ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኒዉ ዮርክ ከተማ የሚገኘዉ የፔን አሜሪካ ማእከል በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበር በፅናት የሚታገለዉና ካለፈዉ መስከረም ወር 2011 ጀምሮ በመለስ መንግሰት በሽብርተኝነት ተከሶ በእስር ላይ የሚገኘዉ ጋዜጠኛና ፀሃፊ እስክንድር ነጋ የዘንድሮዉ የ2012 አለምአቀፍ የባርባራ ጎልድ-ስሚዝ ተሸላሚ  እንዲሆን ወሰነ። 

የፀረ ሽብር ህጉ መንግሰት “ሽብርተኛ” በማለት የሚገምታቸዉን ቡድኖች “ያበረታታሉ” ወይንም “ የሞራል ድጋፍ ይሰጣሉ” የሚላቸዉን ለመወንጀል እንደሚጠቀምበት በመግለፅ በጋዜጠኛ እስክንድር ላይ የተመሰረተዉ ክስ ጥፋተኛ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ እስከሞት ሊያስፈርድበት እንደሚችል ፔን አስረድቷል።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስከበር በሚያደርጉት ትግል ለክስና እስራት የሚዳረጉ የዚህ አለም አቀፍ ሽልማት አሸናፊዎች የተዘጋጀላቸዉን ሽልማት የሚቀበሉት እኤአ በመጪዉ ግንቦት 1 ቀን 2012 በኒዉ ዮርክ ከተማ በአሜሪካን የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ዉስጥ በሚካሄድ ስነ ስርኣት ላይ እንደሚሆን ታዉቋል።

“ ኢትዮጵያዊዉ ፀሃፊ እስክንድር ነጋ ብዕሩን ሲያነሳ የሚፅፋቸዉ ነገሮች  እራሱን አደጋ ላይ ሊጥሉት እንደሚችሉ በርግጠኝነት የሚያዉቅ፤ ከፀሃፊዎች ሁሉ በጣም ደፋርና የሚደነቅ ነዉ” በማለት ገልፀዋል፤ የአሜሪካን ፔን ማዕከል ፕሬዝዳንት፤ ፒተር ጎድዊን።

“ ከሞላ ጎደል ያደረገዉ ይህንኑ ነዉ። እናም በኢትዮጵያ “የፀረ ሽብር” ህግ መሰረት ጠንካራ ትችቶች በወንጀለኛነት ሊያስፈርጁ እንደሚችሉ እያወቀ እራሱን ሰለባ ያደረገ ነዉ። እስክንድርን ዝም ለማሰኘት የመለስ ዜናዊ መንግስት ለእስር ሲዳርገዉ ይህ በትንሹ ለ7ኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ።  ይሁንና እስክንድር ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት ባለዉ የመንፈስ ፅናት ገፍቶበታል።  ይህ ተወዳዳሪ የሌላዉ ድፍረት እስክንድር ነጋን የፔን ባርባራ ጎልድ-ስሚዝ የፅሁፍ ነፃነት ሽልማት የሚገባዉ ተሸላሚ ያደርገዋል።” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ላሪ ሲምስ የፅሁፍ ነፃነት ፕሮግራም ዳይሬክተር በኒዉ ዮርክ የሽልማቱ አሸናፊ መሆኑን በገለፁበት  ንግግር “በፅሁፍ በመጠቀም ጋዜጠኛ ወገኖቹንና ዜጎቹን በመወከል በድፍረት የተሟገተ…” በማለት እሰክንድርን አሞግሰዉታል።”

በመቀጠልም “ስለሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ አስፈላጊነትና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም ያለአግባብ እንዲታፈኑ ስለተደረጉ ሌሎች ጋዜጠኞች እጣ ፈንታ በድፍረት የፃፈ፤ አሁንም በራሱ ላይ ተመሳሳይ እጣ ቢደርስበትም ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ እስር ቤት ሆኖ በመታገል ላይ የሚገኝ ሰዉ ነዉ። በእዉነትም ልዩ ሰዉ ነዉ፤ ይሄንን የክብር ሽልማት ልንሰጠዉ በመቻላችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል።

ሲምስ እና ጎድዊን በጋራ በኢትዮጵያ ያለዉ የፀረ ሽብር ህግ ጋዜጠኞችን ኢላማ ያደረገና ህጋዊ ስራቸዉን እንዳያከናዉኑ የሚያደርግ በመሆኑ በስራ ላይ እንዳይዉል፤ በአገሪቱ ያለዉ የማያቋርጥ የፕሬስ ነፃነት ረገጣ በጣም ጎልቶ የሚታይ ምልክት የሆነዉን  እስክንድር ነጋን እና ብሄራዊ ፀጥታን ምክንያት በማድረግ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸዉን በመፃረር ለእስር የዳረጋቸዉን ጋዜጠኞች እንዲፈታ የኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ላይ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

___________________________________________________________________________________________________ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide