ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተቀጣ

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በፌዴራል አቃቤ- ሕግ አቤቱታ የቀረበበት የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የሁለት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ትናንት ከሰዓት በኋላ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ተፈረደበት፡፡  

ፍርድ ቤቱ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኘውን 5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ከማረሚያ ቤት እንዲመጣ በማድረግ የስምንት ወር እስር የበየነበት ሲሆን የነጋድራስ ጋዜጣን ዋና አዘጋጅ ሱራፌል ግርማን በነፃ አሰናብቷል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ሱራፌል ግርማ ትናንት ጠዋት ችሎት ቢቀርቡም ፍርድ ቤቱ 5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ለምን አልቀረበም ሲል የማረሚያ ቤት ተወካይን ጠይቆ፣ ተወካይዋ “እርሱ በአስረጅነት ስለተጠራ መምጣት ያለበት ስላልመሰለኝ ነው፣ የኔ ጥፋት ነው ከሰዓት በኋላ አመጣዋለሁ” በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ችሎቱን ለቀኑ 8፡30 ሰዓት አስተላልፏል፡፡

ችሎቱ በከሰዓት በኋላ ቆይታው የአበበ ቀስቶን ከማረሚያ ቤት መምጣት አረጋግጦ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የአቀረበውን አቤቱታዎችና የጋዜጠኞቹ መልስ በቁንጽል ካሰማና አቶ ክንፈ ሚካኤልም የሰጡትን ጽሁፉ የኔ የራሴ ነው ማለቱን ተናግሮ  ትዕዛዝ  ማስተላለፉን ገልጾአል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤት ዘገባና አፃፃፍን መመርመሩን ገልፆ ጋዜጦቹ ያስተናገዷቸውን ጽሑፎች በሦስት ከፍሎ መመልከቱን አብራርቷል፡፡ “በችሎት በቀጥታ እየታየ ያለ ነገሮችን መዘገብ” ፣ “በችሎት መታየቱ ያበቃ ነገሮችን ዘገባ” እና “በችሎት የሚታዩትን ጉዳዮች ተንተርሶ የሚዘገቡ” ዘገባዎች በማለት ከፍሎ ማየቱን ጠቅሶ፣ የእስክንድር ነጋን የተከሳሽነት ቃል ተንተርሶ የወጣው የችሎት ዘገባ ሳይጨመር ሳይቀነስ በፍርድ ቤት የተባለው የወጣ በመሆኑ  የዐቃቤ ህግ አቤቱታን ውድቅ አድርገነዋል፣ በዚህ ሁለቱም ጋዜጦች ነፃ ናቸው ብሏል፡፡ በዚህም የነጋድራስ ጋዜጣን ዋና አዘጋጅ በነፃ ተሰናብቷል።

በሁለትኝነትም ችሎት የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣው የአንዷለም አራጌን ጽሑፍ ተመልክቷል። በዚህ ጉዳይ ላይም ተከሳሽ አንዷለም አራጌ በማረሚያ ቤቱ ላይ አቤቱታ አቅርበው ማረሚያ ቤቱም መልስ እንደሰጠበት የታወቀ ነው ስለዚህ ይሄ ጽሑፍ በፍርድ ቤቱ ላይ ምንም ችግር አይፈጥርም በማለት ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ  በችሎት እየታየ ባለ ጉዳይ ላይ የተፃፈው የናትናኤል መኮንን እና የክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ጽሑፍ የሚመለከት ነው ያለ ሲሆን፣ ናትናኤል ክርክሩን ከፍርድ ቤት አውጥቶ ወደ ጋዜጣ መውሰዱን፣ ተከሳሽ ይህን ያወጣው ፍርድ እንዲሰጠው አለመሆኑን ፤ አበበ ቀስቶ ደግሞ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ የህግ አመኔታ እንዳያገኝ ያደረገ በመሆኑ  የፍትህ ጋዜጣን ተጠቅሞ የፍርድ ቤት ሥራን በማወኩ ጥፋተኛ ነው ብሏል ፡፡

በዚህ የተነሳ የአበበ ቀስቶ ድርጊት ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት የሚያስቀጣና በገንዘብም 3 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የ8 ወር እስራት በይኖበታል በማለት የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ ውሳኔውን አንብበዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዋና አዘጋጅ እንደመሆኑ የፕሬስ ሥራ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ይሄን በአግባቡ ባለመወጣት በእስር እስከ አንድ ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ቢሆንም የጋዜጣውን ህዝባዊ የፕሬስ ሥራ አገልግሎት ከግምት በማስገባት እስራቱ ወደ ገንዘብ እንዲቀየር በመወሰን  2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል ብሎአል።

ችሎቱ ከተበተነ በኋላም ሁለት ሺህ ብር የመክፈሉ ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለአንድ ሰዓት ያህል በፍርድ ቤቱ ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ የእሥረኞች ማቆያ የብረት ፍርግግ ውጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የሥራ ባልደረቦቹ ሁለት ሺህ ብሩን በባንክ ሲፒኦ አስገብተው ሲያጠናቅቁ ተፈቷል፤ በርካታ ሰዎችም መፈታቱን ሲጠባበቁ ተስተውሏል፡፡

ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ዓርብ ሚያዚያ 19 ቀን 2004 ዓ.ም “ማቆሚያና ገደብ ያጣው የምስኪኗ እናቴ እንባ” በሚል በፍትህ ጋዜጣ የወጣው ጽሑፉ የእርሱ ስለመሆኑ እንዲያሰድረዳ ችሎት እንዲቀርብ በተደረገበት ጊዜ “አዎን! በጋዜጣው ላይ የፃፍኩት የእኔን የግል እምነትና አስተሳሰብ ነው የምጠየቅበትም ከሆነ እኔ ልጠየቅ” ማለቱ ይታወሳል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide