መንግስት ድምጻችን ይሰማ የሚሉ ወጣቶችን ማሰር ጀመረ

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-ከወራት በፊት በአወልያ የተነሳው የእምነት ነጻነት ይከበር ጥያቄ እየተስፋፋ ሄዶ መላው አገሪቱን እያዳረሰ ባለበት ሰአት መንግስት በአንዳንድ አካባቢዎች የሀይል እርምጃ መውሰድ ጀምሮአል።

በምእራብ አርሲ ዞን አሳሳ ወረዳ 4 የእስልምና እምነት ተከታዮች በፌደራል ፖሊስ አባላት ከተገደሉ በሁዋላ ፣ ጥያቄውን አነሱ ሙስሊሞችን ማዋከብና ማሰሩ ቀጥሎአል።

በአወልያ በተነሳው ተቃውሞ ወቅት የተመረጡ የሙስሊሙ አመራሮች፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ለመነጋገር ቀነ ቀጥሮ ጠይቀው እስካሁን ምንም መልስ ባለማግኘታቸው እያዘኑም ቢሆን በሰላማዊ ትግሉ ለመግፋት በወሰኑበት ወቅት፣ መንግስት ሆን ብሎ ተቃውሞውን በሀይል ለመጨፍለቅ እንቅስቃሴ መጀመሩ ፣ ሙስሊሙን ማህበረሰብ እያስቆጣ ነው።

በነገው እለት በአዲስ አበባ ለቡ ኢምራን መስጂድ ውስጥ እረብሻ አስነስተዋል የተባሉ በእስር ላይ የሚገኙ 10 ወጣቶች በፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ላይ ይቀርባሉ። ወጣቶቹ የቀረበባቸው ክስ የእስልምና መንግስት እስኪቋቋም እንታገላለን በማለታቸው እና የመጅሊስ አባላትን “እናንተ የቆማችሁት ለመንግስት ፖለቲካ ነው፣ የመንግስት አጫፋሪዎች ናችሁ” በማለት ተናግረዋቸዋል ተብሎ ነው።

 በሌላ ዜና ደግሞ በአሳሳ ወረዳ በ4 ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ሙስሊሞቹ በፖሊስ ጣባያው ላይ ጥቃት ለመፈጸም በመሞከራቸው ነው ሲል መንግስት አስታውቋል።

ብሉምበርግ የመንግስትን ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ ሽመልስ ከማልን ጠቅሶ እንደዘገበው እርምጃው የተወሰደው ህዝቡ አንድ በእስር ላይ የሚገኙ የሀይማኖቱን መሪ ለማስፈታት ሙከራ በማድረጉ ነው። 10 ፖሊሶች መቁሰላቸውን፣ የፖሊስ ጣቢያውና የፖስታ ቤቱ መቃጠላቸውን ፣ እንዲሁም ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 24 ሰዎች መታሰራቸውን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል።

 አንድ አክራሪ ኢማም ጂሀድ ለማስነሳት ሲቀሰቅሱ መገኘታቸውን ተከትሎ ፣ ፖሊስ በቁጥጥሩ ስራ ካወላቻው በሁዋላ፣ ደጋፊዎቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቃቸው የተፈጠረ መሆኑን አቶ ሽመልስ ለብሉምበርግ ዘጋቢ ተናግረዋል።

ሌሎች ወገኖች ግን የመንግስት ታጣቂዎች እርምጃውን የወሰዱት አቶ መለስ በቅርቡ የአልቃይዳ ኔት ወርክ አርሲ ውስጥ ተገኝቷል ብለው መናገራቸውን ተከትሎ ነው ይላሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide