ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ባስቻለው ችሎት የጋዜጠኛ ርእዮት አለሙን ዬይግባኝ አቤቱታ ተመለከተ።
የመሀል ዳኛ በላቸው አንሽሶ፣ እና የግራ ዳኛው በንባብ እንደገለጡት ዛሬ መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ለውሳኔ ነበር። ዳኞቹ አሉ የተባሉ መዝገቦችን እንዲቀርቡ አዘው መመልከታቸውን ተናግረዋል። የመሀል ዳኛው ርእዮትን ለፖሊስ ቃሉዋን መስጠቱዋንና ለፍርድ ቤት ደግሞ የተከሳሽነት ቃል መስጠቱዋን የጠየቁዋት ሲሆን፣ ርእዮትም በመጨረሻው ላይ ፖሊስ በሀሰት ከጨመረው ውጭ ሌላው ልክ ነው ብላለች።
ዳኛውም በፍርድ ቤት የሰጠሽው ቃል ትክክል ነው ብለው ሲጠይቋት ” ርእዮትም የሀሰት መረጃዎች ከኢሜሌ እንደወጣ አስመስለው አቅርበዋል፤ እኔ ከታሰርኩ ከ10 ቀናት በሁዋላ የተጻፈን ኢሜል ሁሉ እንደማስረጃ አድርገው አቅርበዋል” በማለት መልሰዋል።
ዳኛው “እነዚህ ያነሳሻቸው ፎቶዎች ምንድ ናቸው?” ብለው ሲጠይቋት፣ ርእዮትም ኤልያስ በመርካቶ አካባቢ በቃ የሚል ጽሁፍ ተለጥፏልና ተመልክተሽ ዘግቢልኝ በማለቱ በቦታው ሂዳ በማረጋጋጥ ፎቶ አንስታ የጋዜጠኝነት ስራዋን ሰርታ መላኩዋን ፣ የአትዮጵያን ሪቪው ድረገጽ ሪፖርተር ሆና መስራቱዋንና ከኤልያስ ጋር በ አርቲስት ደበበ እሸቱ በኩል መገናኘቱዋን ተናግራለች።
ደኛውም ” ከመዝገቡ እንደማየው ኤልያስ ክፍሌ ብዙ ነገር ነው የሚሰራው፣ አቶ ዘሪሁን የተባሉ ሰውን በመጠቀም በሌሊት ወረቀት እያስተላለፈ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አታውቂም ነበር ወይ?’ በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ ፣ ርእዮትም ” እኔ ኤልያስ ክፍሌን የማውቀው በኢትዮጵያን ሪቪው ባለቤትነቱ ነው። ስለእርሱ ሌላ መረጃ የለኝም” በማለት ስትመልስ ዳኛውም ” ይህ ያደረግሽው ወንጀል ነው አይደለም የሚለውን ገና የምናየው ይሆናል ” በማለት ተናግረዋል።
ዳኛው በአቃቢ ወንድማገኝ ምትክ የተተካውን አዱሱን አቃቢ ህግ ” በሙከራ፣ በመተባባርና በመተግበር የሚል ክስ አቅርባችሁዋል፣ ይህ ያቀረባችሁት 3 ክስ ይሆናል እንዴ ብለው ሲጠይቁ ” የወንጀል አፈጻጸሙ በተከታታይ፣ በቡድንና በማበር በመሆኑ ነው፣ ፍርድ ቤቱ በአንድ ይሁን ካለም ችግር የለውም በማለት መልሷል። ዳኛውም ” የክሱ ምክንያት ይህ አይደለም፣ ይህችን ልጅ የከሰሳችሁዋት መረጃ አስተላለፍሽ ብላችሁ ነው አይደለም በማለት በድጋሜ ጠይቀዋል።
ጠበቃ ሞላ ዘገየ ለፍርድ ቤቱ ” የአቶ ኤልያስ ክፍሌና የርእዮት ግንኙነት የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተመሰረተ ነው ያሉ ሲሆን፣ ኤልያስ ክፍሌም በፓርላማ አሸባሪ ተብሎ ያልተፈረጀ ጋዜጠኛ ነው። ብለዋል።
ርእዮት በበኩሏ ከእኔ ጋር አብረው የተከሰሱትን ሰዎች እስር ቤት ነው የማውቃቸው በማለት አክላ ተናግራለች።
የይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ለሀምሌ 27 ቀን 2004 ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide