ፖርላማው የውጪ አገር ሰዎች በኢንቨስትመንት ሲሰማሩ እንደ ኢትዮጽያዊያን እንዲታዩ ሰጥቶ የነበረውን ዕድል አነሳ

ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በፓርላማው አስቸኳይ ጉባኤ ከአገሪቱ የ2005 በጀት ጋር ተያይዞ የጸደቀው የተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ ከዚህ በፊት በትውልድ ኢትዮጽያዊያን ያልሆኑ የውጪ አገር ሰዎች በኢንቨስትመንት ሲሰማሩ እንደ ኢትዮጽያዊያን እንዲታዩ ሰጥቶ የነበረውን ዕድል አነሳ፡፡
አሁን በሥራ ላይ ባለው የኢንቨስትመንት አዋጅ አንቀጽ 37 መሰረት የውጪ ዜጎች አስቀድሞ የጸና የንግድ ሥራ ፈቃድ ፣ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ፣የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት እና ሌሎችም በሕጉ የተቀመጡ መሰፈርቶችን ካሟሉ እንደ አገር ውስጥ ባለሃብት የሚቆጠሩበት አግባብ ነበር፡፡

በዚሁ መሰረት ኢትዮጽያ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በንግድ ሥራ ውስጥ ተሰማርተው በመደበኛነት ይኖሩ የነበሩ እንደአርመን ፣ግሪኮች ፣ሕንዶች፣አረቦችና የእነሱ ጥገኞች ወይም
ወራሾች በኢንቨስትመንት ሥርዓት ውስጥ ገብተው የውጪ ምንዛሪ ከአገር እንዳያወጡ የታሰበ ቢሆንም በተግባር ግን አፈጻጸሙ  ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር ከፍቶ እንደቆየ የጸደቀውን አዋጅ ለማብራራት የቀረበው ሰነድ ይጠቁማል፡፡
በዚሁ መሰረት አዋጁ በይፋ በሌላ አዋጅ ከመሻሩ በፊት ከ2002 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ብቻ እንደአገር ውስጥ ባለሃብት የሚያስቆጥር የምስክር ወረቀት የመስጠቱ ሥራ እንዲቆም ተደርጎአል ይላል፡፡

አዲሱ ማሻሻያ ይህንኑ በአዋጅ ያልተደገፈ ክልከላ የሚያጠናክርና የሕግ ድጋፍ የሚሰጥ ነው፡፡
የቀድሞውም ሆነ የተሻሻለው አዋጅ በትውልድ ኢትዮጽያዊ የሆኑትን ባለሃብቶች እንደምርጫቸው የአገር ውስጥ ወይም የውጪ ባለሃብት ሆነው የሚቆጠሩበትን አሰራር ይፈቅዳል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ብዙ ውጣውረድ ያለው መሆኑን ባለሀብቶች በየጊዜው ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን ምናልባት አሰራሩ ከገዥው ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚነግዱ እንደ ሼህ አልአሙዲ ዓይነት ባለሀብቶችን ለመጥቀም የተቀመጠ እንደነበርና ይህም ተልዕኮው በመጠናቀቁ በተግባር የመከነ ነው ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide