በመንግስት እና በሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል ያለው ፍጥጫ እየጨመረ ነው

ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ባለፈው እሁድ ድምጻችን ይሰማ በማለት ላለፉት ተከታታይ ወራት ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ ሙስሊሞች፣ አርብ እለት የመንግስት ታጣቂዎች በአወልያ የፈጸሙትን ግድያ እና ድብደባ በመቃወም፣ እሁድ እለት ከመንግስት ፈቃድ ወጭ የሰደቃና የአንድነት ዝግጅት ማድረጋቸው መንግስትን በእጀጉ ያስደነገጠና ያስቆጣ ሆኗል።

ባለፈው አርብ፣ ቅዳሜና እሁድ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በጎጃም እና በጅማ መስመሮች ወደ አዲስ አበባ ይጓዙ የነበሩ ሰዎች ከመኪና እየወረዱ መታወቂያቸው እየታየ በተደጋጋሚ ሲፈተሹ ተስተውሏል። የአይን እማኞች እንደገለጡትመታወቂያቸው ላይ የእሰላም ስም ያለባቸው፣ ወይም የእስልምና ምልክት የሆኑ ነገሮችን የለበሱ ወይም የያዙ ሰዎች ከመኪና ላይ እንዲወርዱ እየተደረገ ወደ አስር ቤት ተልከዋል።

የመንግስት ታጣቂዎች በተለያዩ ሙስሊሞች ላይ ስብእናቸውን የሚያዋርድ ስድብና እንግልት ሲያደርሱ መመልከታቸውን ከደሴ ወደ አዲስ አበባ እና ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሰዎች ለኢሳት ገልጠዋል:።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የሰሜን ሸዋ ነዋሪ በእርሱ አካባቢ ከ200 በላይ ሙስሊሞች ከመኪና ላይ ወርደው እየተገፉ ወደ እስር ቤት ሲወሰዱ መመልከቱን ተናግሯል፡፣  ሙስሊሞች ከመኪኖች ላይ እየወረዱ የሌሎች እምነት ተሰፋሪዎች ብቻ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ ሲደረግ መመልከቱን በእለቱ ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ የተጓዘ አንድ ግለሰብ ገልጧል። ይህ ግለሰብ ሙስሊሞች እንዲህ ሲገለሉና ሲዋረዱ አይቼ አላውቅም፣ ወታደሮቹ የፈጸሙት ድርጊት እጅግ በጣም ይዘገንናል፤ እኛ ተመርጠን ወደ መኪናው ተመልሰን እንድንገባ ሲፈቀድልን፣ ሙስሊሞቹ በረሀ ላይ ቀርተዋል። ት እንደወሰዷቸው አላውቅም፤ ምናልባት ሁሉም ወደ አንዋር መስኪድ ላይሄዱ ይችላሉ፣ ለንግድ ስራ ገንዘባቸውን ከፍለው የሚጓዙ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ።” በማለት አክሎ ገልጧል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፣የፌዴራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጄንሲ  የብዙሀን ሙስሊሞችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጋቸውን- “ድምፃችን ይሰማ!”የተሰኘው የሙስሊሞች አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።

እነዚህ ሦስቱ የመንግስት  ተቋማት ባደረጉት የጋራ ስብሰባ ፤ 17ቱ  የብዙሀን ሙስሊም አስተባባሪ ኮሜቴ አባላት የረመዳን ፆም ከመግባቱ በፊት እንዲታሰሩ ውሳኔ ማሳለፋቸውን እንደደረሰበት ኮሚቴው ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል።

በስብሰባው ኮሚቴውን በማሰር ብቻ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ መግታት አይቻልም የሚል ሀሳብ በስፋት ከተንሸራሸረ በሁዋላ፤ከኮሚቴው ጋር በቅርበት  ሆነው የማስተባበር  ሥራ እየሰሩ ያሉ ሰዎችንም ለይቶ ማሰር እንደሚያስፈልግ መወሰናቸውንም ስብሰባውን የተካፈሉ ምንጮች ለኮሚቴው ነግረውታል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአንዋር መስጊድ እና ከአወሊያ ውጪ ባሉ መስጊዶችም  በተመሣሳይ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እና  ሙስሊሙን የሚያስተባብሩ ሰዎችም  እንዲታሰሩ በስብሰባው ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል።

ከሁሉም በላይ በአሁኑ ጊዜ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ያለው የፌስ ቡክ አገልግሎት  በኢትዮጵያ ሊዘጋ ይገባል የሚል አቋም  በሦስቱም ተቋማት ተወካዮች በተደጋጋሚ  መንፀባረቁን የጠቆሙት ምንጮቹ፤ ከሚመለከተው የመንግስት መዋቅር ጋር በመነጋገር የፌስ ቡክን አገልግሎት ለማስቆም ውሳኔ ማሳለፋቸውንም አመልክተዋል።

“ድምፃችን ይሰማ” ባሰራጨው በዚሁ ጽሁፍ፦”ኮሚቴዎችንም ሆነ ሌሎች አስተባባሪዎችን በማሰር፤ የሙስሊሙን መብት መብት የማስከበር እንቅስቃሴ ከቶውም  ማቆም እንደማይቻል ሁሉም ወገን ሊረዳው ይገባል ብሏል።

ኮሚቴው ዘግይቶ ባሰራጨው ወረቀት ደግሞ ባለፈዉ እሁድ የፌደራል ፖሊስ በአወልያ ቅጥር ግቢ ዉስጥ እጅግ በርካታ የጦር መሳሪዎችን ማስገባቱን በማስታወስ፤ መሳሪያዎቹን  በአወልያ ግቢ ዉስጥ ፖሊሶች ሲፈትሹ እንዳገኟቸው በማስመሰል  በ ኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ ለማስተላለፍ ቪዲዮ ቀረፃው  ተጀምሯል ብሏል።

ፖሊሶቹ  የአወልያ የጥበቃ ሰራተኞችን ደብድበዉ ካባረሩ ቡሀላ  ወደ ግቢው በመግባት ራሳቸው ይዘውት የመጡትን መሳሪያ  በቪዲዮ እየቀረጹ እንደሆነ ያጋለጠው ኮሚቴው፤ “ የቀረፃው ዓላማ በሰደቃዉ ፕሮግራም ላይ የሙስሊሙ ኮሚቴዎች ህዝቡን ሊያስታጥቁበት የነበረዉን መሳሪያ በቁጥጥር ስር አዉለናል” በማለት  “አኬልዳማ ቁጥር 3” ድራማን በኢቲቪ ለማቅረብ እንደሆነ ተደርሶበታል ብሏል።

“ፖሊስ ለምን ወደ መስጊድ ገባ?“ በማለት ህዝበ-ሙስሊሙ በተቆጣበት ሰዓት የዚህ ዓይነት የተንኮል ድራማ እየተሰራ ያለው ከተጠቀሰው ምክንያት በተጨማሪ፦”ፖሊስ ወደ መስጊድ የገባው የሙስሊሙ ኮሚቴ አስተባባሪዎች የጦር መሳሪያ ወደ መስጊድ እንዳስገቡ ጥቆማ ስለደረሰው ነው” የሚል ውሀ የማይቋጥር  ፕሮፓጋንዳ በኢቲቪ ለማሰራጨት ጭምር እንደሆነ ከምንጮቹ መገንዘቡን ኮሚቴው ጠቁሟል።

በዛሬው እለት የአህሉሱና ወልጀመአ ኡላማዎች ሴሚናር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች መንግስት ህዝብንና ሀገርን ከጽንፈኞች ድርጊት ይጠብቅ በማለት መናገራቸውን የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

በመንግስትና በሙስሊሙ ማሀበረሰብ መካከል እየጨመረ የመጣው ፍጥጫ ወደ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀረ ታዛቢዎች ይገልጣሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግንቦት7፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲና የኢትዮጵያ የአንድነትና የፍትህ ንቅናቄ በጋራ የመሰረቱት ጥምረት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ያደረሰውን ጥቃት በጽኑ አውግዟል።

ጥምረቱ ባወጣው መግለጫ፣ የመለስ አገዛዝ የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ሰለማዊና ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲፈታ፣ የታሰሩትን እንዲለቅ እንዲሁም ታጣቂዎቹን ከአምልኮ ቦታዎች እንዲያርቅ ጠይቋል። አለማቀፉ ማህበረሰብ በሙስሊሙ ላይ የተፈጸመውን ግፍ እንዲያወግዝ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከሙስሊም ወንድሞች እና እህቶች ጎን በጋራ እንዲቆሙ ጠይቋል።

በተመሳሳይ መንገድም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች የጠየቁት መሰረታዊ የእምነት ነጻነታቸው እንዲከበርና የሀይማኖቱን መሪዎች ያለምንም የመንግስት ጣልቃ ገብነት፣ በራሳቸው መምረጥ እንዲችሉ ሆኖ እያለ አገዛዙ ፖሊሱንና ነጭ ለባሾችን አዝምቶ መብታቸውን በሰላም የጠየቁትን ዜጎች በሀገር ላይ ደባ እንደፈጸሙ በማስመሰል ጭካኔ የተሞላበት ጉዳት ማድረሱን አውግዙዋል።

ሸንጎው  ” ምግብ በማብሰል የተሰማሩትን በሌሊት ከቦ አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት ምእመናኑን መደብደቡን፣  ማሰቃየቱን፣ ማሰሩንና ማቁሰሉን ” በእጅጉ ተቃውሟል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide