ጆሴፍ ኮኒን ለማደን የተሰራጨው ፊልም ኢንተርኔትን አጨናነቀ

መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የህፃናት ቀበኛ የሆነውን ጆሴፍ ኮኒን ለማደን የተሰራጨው ፊልም በአራት ቀናት ብቻ በ60 ሚሊዮን ጎብኝዎች በመታየት የኢንተርኔት መስመሮችን ማጨናነቁ ተዘገበ ።

 ሰሞኑን የተሰራጨው ይህ ፊልም እንደሚያስረዳው፤ የኡጋንዳው የጎሬላ ተዋጊና የ”ጌታ ተጋዳይ ሠራዊት” (ሎርድ’ስ ሬዚዝታንስ አርሚ) መሪ ጆሴፍ ኮኒ፤ በኡጋንዳ ከ 60 ሺህ በላይ ህፃናትን ጠልፏል።

 ኮኒን ለማደን በዩቲዩብ የተሰራጨውና በጥቂት ቀናት ወደ 60 ሚሊዮን በሚጠጉ ተመልካቾች በመጎብኘት የኢንተርኔት መስመሮችን ያጨናነቃው   የ30 ደቂቃ ቪዲዮ ፊልም  ዋነኛ ዓላማ፤ ጆሴፍ ኮኒን በአረመኔነቱና በጭካኔው  በዓለም ላይ ታዋቂ በማድረግ በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው ተብሏል።

ላለፉት ሁለታ አስርት ዓመታት  ሕፃናትንና ወጣቶችን አስገድዶ በመጥለፍ ሴቶቹን ለወሲብ ባርነት ፤ ወንዶቹን ደግሞ ለወታደርነት ሲዳርግ እንደቆየ የሚነገርለት ጆሴፍ ኮኒ፤  በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ  ቁጥር አንድ ታዳኝና ተፈላጊ  ከሆኑት  ጨካኝ ሰዎች መካከል  አንዱ  ሆኗል።

ጆሴፍ ኮኒ በ 20 ዓመታት ውስጥ  ከ60 ሺህ በላይ ሕፃናትን ጠልፏል። ”ኮኒ 2012” የተሰኘውን ይህን ቪዲዮ ያሰራጨው መሰረቱን ሳንዲያጎ ያደረገው “ኢንቪዚብል ችልድረን” የተሰኘ ድርጅት ነው። የድርጅቱ መስራችና የፊልሙ ዳይሬክተር ጄሰን ሩሰል፤ የቪዲዮው ዓላማ ጆሴፍ ኮኒን በዓለም ላይ እጅግ ታዋቂ በማድረግ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ጀምስ ሩስል አክለውም ፦” ኮኒ ታዋቂ እንዲሆን ነው ዓላማችን።ታዋቂነቱ ግን እንዲወደስና እንዲፈቀር ለማድረግ አይደለም።   ይልቁንም የጆሴፍ ኮኒን የጭካኔ ማንነት  በዓለም አቀፍ ደረጃ  በማሳወቅና የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማብዛት፤ ግለሰቡን አድኖ በመያዝ ለዓለም  ፍርድ ቤት እንዲቀርብ እና በኡጋንዳ ሕፃናትና ወጣቶች  ላይ እየተፈጸመ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር ለመታደግ ነው”ብለዋል። 

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide