ሰመጉ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና መታሰራቸውን አስታወቀ

የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ላለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ አለማቀፍ እውቅና ያተረፈው ቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ( ኢሰመጉ) ወይም አሁን ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ( ሰመጉ) እየተባለ የሚጠራው ድርጅት ባወጣው  35ኛ መደበኛ ጉባኤ በአገሪቱ ውስጥ ባለፈው አንድ አመት የታየቱን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አውጥቷል።

በሪፖርቱ መሰረት በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በቆንሴ አርኪ ገበሬ ማህበር ወ/ሮ ወርቄ አሩሳ የተባሉ ሴት የግል ንብረታቸው የሆነውን 20 ሺ ብር የሚያወጣ ባህር ዛፍ ለቀበሌው ሊቀመንበር በ3000 ሺ ብር በህገወጥ መንገድ እንዲሸጥ ተደርጎ ዛፉ በሚቆረጥበት ወቅት ተቃውሞ በማቅረባቸው የፖሊስ ባልደረባ የሆነው ፈቃዱ በሁለት ጥይት ገድሎአለቸዋል።

በጉጂ ዞን በአዶላ ወረዳ በአንፈራራ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆኑ የጌዲዮ ብሄረሰብ ተወላጆች ኑሮአቸውን የሚደጉሙበትን  ቡና ፣እንሰት ና ሙዝ የመሳሰሉትን ተክሎች  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የወረዳው ባለስልጣናት እና ፌደራል ፖሊስ ከጥቅምት 1 እስከ ጥቅምት 6፣ 2003 ዓም በግፍ ጨፍጭፈው ነዋሪዎች እንዳይጠቀሙበት አድርገዋል። ሁኔታውን ለመቃወም የወጡት ነዋሪዎች በአድማ በታኞች በጥይት፣ በድብደባ እና በእስር እንዲበተኑ ተደርጓል።

ኢንጂነር በአካል ተሾመ በተባሉት ላይ ደግሞ በ1997 ምርጫ በተቃዋሚዎች ቅስቀሳ ላይ ተሳትፈሀል ተብለው ሲዋከቡ ቆይተዋል። በ1999 ዓም የኢሰመጉን ድረገጽ ሲያዘጋጁ ነበር። ድረገጹ በአየር ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የደህንነት ሀይሎች ድረገጹን እንዲያቆም እንዲያደርግ ሲያስፈራሩትና ሲዝቱበት ከቆዩ በሁዋላ ከኢሰመጉ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲቀንስ አድርገውታል።  ይሁን እንጅ የመንግስት ስራ ለመቀጠር ሲያመልክት እንዳትቀጥሩት ተብለናል በሚል ስራ ሳያገኝ ቆይቶ በአንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ የስራ እድል ባገኘበት ጊዜ የደህንነት ሀይሎች  ቀን ላይ ሲከታተሉት ከቆዩ በሁዋላ መኪናውን ገጭተው ያለጠያቂ ሄደዋል። ኢንጂነር በአካል እና ኢንሹራንሳቸው ከፖሊስ ሪፖርት ለማግኘት ሲሄዱ፣ ከዚህ እንዳትደርሱ አንደተባሉ፣ አንድ ቀን ከኢሰመጉ ቢሮ ሲወጡ ፣ ከድርጅቱ ጋር ያለህን ስራ የማታቆም ከሆነ በአንተም ሆነ በባለቤትህና በእህትህ ህይወት ላይ ፍረድ በማለት አስጠንቅቀውታል።

ሰመጉ በሪፖርቱ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚገኙትን ሰዎች  ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። በአማራ ክልል የመኢአድ አባላት የሆኑት ወጣቶች ታደሰ መለሰ፣ እስክንድር መላኩ፣ መለስ ስጠኝ፣ አሸናፊ አየለ፣ ማንደፍሮ አካልነው እና ቴዎድሮስ አያሌው በማእከላዊ ታስረው ሲገኙ፣ በኦሮሚያ ደግሞ አቶ ደሳለኝ ደበል፣ ተስፋ ሞተራ፣ ሳምሶን አለሙ፣ በላይ ከርሜ፣ ኢታና ሰንበቶ ነጋሽ ኩሽ እና ኑራ በድሩ በቃሊቲ ታስረው ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ተለቀዋል።

በፖሊስ ተይዘው በህገወጥ መንገድ ከታሰሩት መካከል መ/ር ቀኖ ማቲዎስ፣ አቶ መንግስቱ ሞሲሳ፣ አቶ አያና ቀበታ፣ አቶ ኩመራ ሰንበታ እና አቶ ታየ ዳምጠው ይገኙበታል።

በኢሰመጉ ሪፖርት ላይ አቶ መላኩ በየነ የተባሉት ግለሰብ የደረሰባቸው ስቃይም ተመልክቷል። ግንቦት19/2003 ዓም ኦሎምፒያ አካባቢ ከረጅም ጊዜ በፊት ገንዘብ አበድሬዋለሁ ያሉትን  ሰለሞን ተካልኝን ገንዘቤን ስጠኝ ብለውት ስለከለከላቸው ከሀዲ ብለው ሰድበውት ሄደዋል። የአቶ መላኩ የመኪና ሰሌዳ ለትራፊክ ፖሊስ እንዲበተን  ከተደረገ በሁዋላ አቶ ሰለሞን ተካልኝ ክስ መስርቶብሀል ተብለው ተይዘዋል። በመጀመሪያ በስምምነት እንዲጨርሱ ተብሎ የዋስ መብታቸው ተጠብቆላቸው እንዲወጡ ዋስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ወደ ሌላ ፖሊስ ጣቢያ እንዲዛወሩ ተደርጓል። በቂርቆስ ክፍለከተማ ፖሊስ ጣቢያ አቶ መላኩ ሌሊቱን ሙሉ በጨለማ ቤት ወስጥ አድረው ሲመረመሩ ከቆዩ በሁዋላ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረዋል። በተለያዩ ጊዜያት በደረሰባቸው  ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እና ስቃይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በመጨረሻም አቶ መላኩ ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ ማስረጃ ባለማቅረቡ በዋስ ተለቀዋል።

በሪፖርቱ ውስጥ በደህንነት ሀይሎችና በፖሊስ በርካታ ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ተካትቶአል። ኢሳት ሙሉውን ሪፖርት ሰሞኑን ያቀርባል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide