ዶናልድ ትራምፕ ወታደራዊ ሰልፍ እንዲዘጋጅ ጠየቁ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2010)

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በዋሽንግተን ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ/ፓሬድ/እንዲያዘጋጅ ጠየቁ።

በፕሬዝዳንቱ የቀረበው የወታደራዊ ትዕይንት ጥያቄ ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ባለፈው አመት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው የፈረንሳውያኑ አመታዊ ባስቲል ዴይ ወታደራዊ ሰልፍ ላይ ተገኘተው የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወታደራዊ ሰልፉን “በሕይወቴ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ወታደራዊ ሰልፍ አይቼ አላውቅም” በማለት ገልጸውት ነበር።

ስለፈረንሳዩ ሰልፍ አድናቆታቸውን የገለጹት ዶናልድ ትራምፕ በዋሽንግተን ተመሳሳይ ትዕይንት እንዲካሄድ የሀገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎንን መጠየቃቸው ተሰምቷል።

የፕሬዝዳንቱ ጥያቄ ብዙዎችን ሲያነጋግር ፣ተቃውሞዎችንም በማስተናገድ ላይ መሆኑን የተለያዩ የዜና ምንጮች በመዘገብ ላይ ናቸው።

በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየታቸውን የሰጡት የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ እቅዱ ለአሜሪካውያን ጀግኖች ክብር ለመስጠት እንደሆነ አመልክቷል።

“ዘወትር የሃገራችንን ደህንነት ለማረጋገጥ መስዋዕትነት ለሚከፍሉት አሜሪካውያን ዶናልድ ትራምፕ ትልቅ አክብሮት አላቸው” ሲሉ ሳንደርስ አስተያየታቸውን አክለዋል።

“ስለሆነም ሁሉም አሜሪካውያን ለነዚህ ባለውለታዎቻችን አድናቆትና አክብሮታቸውን እንዲገልጹ ሲባል ወታደራዊ ሰልፉ ወይንም በእነሱ አጠራር ፓሬዱ መታቀዱን ገልጸዋል።

ቀን ያልተቆረጠለትና ገና ከሃሳብ ብዙም ፈቀቅ ያላለው እቅድ ከወዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የሀገሪቱን ርዕሰ መዲና የጦር ቀጠና ማስመሰሉ ምን ይፈይዳል የሚለውን ጨምሮ ሰልፉ ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል የሚሉት ለተቃውሞው ምክንያት ሆነዋል።

እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ ከሆነ የተለያዩ አስተያየቶችን እያስተናገደ ያለው የወታደራዊ ሰልፉ ሃሳብ ቅድመ ዝግጅት ከአሁኑ ተጀምሯል።

የፈረንሳዩ ባስቲል ደይ ወታደራዊ ሰልፍ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1980 ጀምሮ በየአመቱ የሚካሄድ በአል ነው።