ከ700 የሚበልጡ እስረኞች እንዲፈቱ ተወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2010)

ላለፉት 7 አመታት ያህል በወህኒ የቆዩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ከ700 የሚበልጡ እስረኞች እንዲፈቱ መወሰኑን የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ጠቅላይ አቃቢ ህግን ጠቅሰው መገናኛ ብዙሃኑ እንደዘገቡት በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው እስረኞች ቁጥር በአጠቃላይ 746 ናቸው።

ከመስከረም 3/2004 ጀምሮ በወህኒ ቤት የሚገኙት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ ከተፈቺዎቹ ውስጥ በስም ተጠቅሰዋል።

ነገር ግን ስለሌሎቹ ተፈቺዎች የተገለጸ ነገር የለም።

ተፈርዶባቸው በወህኒ ቤት ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ 417ቱ በይቅርታ እንዲፈቱ የይቅርታ ቦርድ መወሰኑ ተገልጿል።

ለፊርማ ወደ ፕሬዝዳንቱ መሄዱም ተመልክቷል።

ክሳቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ 329 እስረኞች ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥና ከእስር እንዲለቀቁ ተወስኗል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት እየተካሄደ ነው በተባለው እስረኞችን የመልቀቅ ተግባር በይቅርታ ከሚለቀቁት 417 እስረኞች 298ቱ ከፌደራል ወህኒ ቤት መሆናቸው ታውቋል።

119ኙ ደግሞ በአማራ ክልል የታሰሩ መሆናቸው ይፋ ሆኗል።

ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው ደግሞ 278ቱ ከፌደራል ወህኒ ቤት ሲሆን 18 ከአማራ ክልል እንዲሁም ከትግራይ ክልል ደግሞ 33 እንደሆኑም ተመልክቷል።

እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌን ጨምሮ 417ቱ እስረኞች ከፕሬዝዳንቱ ፊርማ በኋላ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ይፈታሉ ብለዋል መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው።

እስረኞቹ በትትክል መቼ ይፈታሉ ለሚለው ግን ቀን አልተቆረጠለትም።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ውስጥ ቀደምት ከነበሩት ጋዜጠኞች አንዱ ሲሆን ሃሳቡን በአደባባይ በመግለጹ ለ8 ጊዜያት ያህል በተደጋጋሚ የታሰረ ሲሆን ከ7 ከሚበልጡ አለምአቀፍ ተቋማት የፕሬስ ነጻነት ሽልማትን ተቀዳጅቷል።

እስክንድር ነጋ የተፈረደበት የ18 አመታት እስራት ነበር።

የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበረው አቶ አንዱአለም አራጌ በምርጫ 1997 የቅንጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረና ወደ ወህኒ ከተጋዙ ፖለቲከኞችም አንዱ ነበር።

ሁለት አመታት ያህል በወህኒ አሳልፎ ከወጣ በኋላ እንደገና በአሸባሪነት ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ከመስከረም 3/2004 ጀምሮ በእስር ቤት ቆይቷል።

በእስር ቤት ቆይታው ሁለት መጽሀፍትን ጽፎ ለንባብ አብቅቷል።

አንዱአለም አራጌ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

በእስክንድርም ሆነ በአንዱአለም ላይ እንደሌሎቹ ብዙዎች እስረኞች ምንም ነገር በሌለበት በግፍ ፍርድ እንደተወሰደባቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በወህኒ ቤት ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ጄኔራል አሳምነው ጽጌ፣ኮለኔል ደመቀ ዘውዱና ሌሎችም ይገኙበታል።