የበይነ መረብ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2010)

በአለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ግብረሃይል የተጠራውን የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻ ለማጠናከር ዛሬ የበይነ መረብ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆኑ ታወቀ።

ዘመቻው ፌስ ቡክንና ቲውተርን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ መረጃ መረቦች መጀመሩ ተገልጿል።

የዘመቻው አላማ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ህዝብን ለመግደልና ለመጨቆን የሚጠቀምበት መሆኑን ለማሳወቅና የዘመቻውን አስፈላጊነት ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በስልጣን ላይ ያለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሃት ውጪ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያገኘው አመታዊ የውጭ ምንዛሪ መጠን 4 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህም በእርዳታ፣በብድርና በቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከወጭ ንግድ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ የሚልቅ እንደሆነም ይነገራል።

ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ገንዘብ በቀጥታ ለልማትና እድገት ከመዋል ይልቅ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ህዝባችንን ለመግደል፣ ለማፈንና ለማሰቃየት በሚል ላቋቋማቸው የጸጥታና ደህንነት መስሪያ ቤቶች የሚውል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ግብረ ሃይል “ገዳዩን ስርአት እናስርበው” በሚል መሪ ቃል የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻ ከከፈተ አንድ ወር ሆኖታል።

ኢትዮጵያውያን በሚልኩት ገንዘብ ለወገናቸው ሞትና ስቃይ በመተባበር ላይ መሆናቸውን አውቀው መቀነስ አልያም ላልተወሰነ ጊዜ ማቆም እንዲችሉ የተከፈተው ዘመቻ ለሶስት ወራት የሚቆይ ነው።

በእስካሁኑ ሂደት ከፍተኛ ውጤት እየታየ እንደሆነ የሚገልጹት የዘመቻው አስተባባሪዎች ህዝቡ አሁንም ዘመቻው እንዲሳካ እያደረገ ያለውን አስተዋጾ አጠናክሮ እንዲቀጥል ይጠይቃሉ።

ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጪያ የተለየ ዘመቻ ዛሬ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቲውተር፣በፌስ ቡክና በሌሎች ማህበራዊ የመረጃ መረቦች ለአንድ ቀን በሚቆየው ዘመቻ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በሀገር ቤት ወገናችን ላይ የሚደርሰውን በደልና ስቃይ ለማሳየት የሚያስችሉ መረጃዎች በመቅረብ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በአማርኛና በኦሮምኛ በተዘጋጁ መልዕክቶች እየተላለፈ ባለው መልዕክት አገዛዙ ለጭቆና የሚያውለው  ገንዘብ እንዲቆም ተጠይቋል።

የዘመቻው አስተባባሪዎች በፌስ ቡክና በቲውተር የሚተላለፉትን መልዕክቶች ኢትዮጵያውያን በማሰራጨት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አድርገዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በስልጣን ላይ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሕወሃት መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሰቃየት ላይ ነው።

ዋዜማ ሬዲዮ የሃገር ቤት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበውም በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ 35 ብር ደርሷል።

ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ብቻ ያለው አገዛዙ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በኢትዮጵያውያን የተጀመረው የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻም ውጤት እያሳየ ነው ተብሏል።