ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዶ/ር ኢሌኒ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እርሳቸውና አብረዋቸው ሢሰሩ የነበሩት የሥራ ባልደረቦቻቸው በፈቃዳቸው ሀላፊነታቸውን እንደለቀቁ አስታውቀዋል።
ሀላፊነታቸውን የለቀቁትም፤ ቦታውን በዘርፉ ልምድ ላካበቱ ሙያተኞች ለመልቀቅ በመፈለጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ዶ/ር ኢሌኒ ሥራ መልቀቃቸውን ፦”የመተካካት ሂደት ነው” ቢሉትም፤ ሁኔታው በገዥዎቹ መንደር ሳይቀር ድንጋጤ መፍጠሩን ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተሉ ጋዜጠኞች ጠቁመዋል።
እንደ ምንጮች መረጃ ፤ሁኔታው ለብዙዎች እንቆቅልሽ የሆነው፤ ዶ/ር ኢሌኒ በቅርቡ በካምፕ ዴቪድ በተካሄደው የ ቡድን 20 አገሮች ስብሰባ ላይ በተሳተፉ እና ከዚያም “ላከናወኑት ተግባር” ተብለው ሽልማት በተበረከተላቸው ማግስት ከሥራቸው መልቀቃቸው ነው።
አንዳንዶች፤ዶ/ር ኢሌኒ በተመደቡበት ሀላፊነት ጥሩ ሥራ እንደሠሩ ሲመሰክሩላቸው፤ ብዙዎች ግን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በጥቅም በመመሳጠር ሙስና ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ነበር በማለት ይከሷቸዋል።
ሥራ አስኪያጇ በተለይ በቡና ግብይት ውስጥ ከመንግስት ሰዎች ጋር በመሆን ነጋዴዎችን ሲያስለቅሱ ፣ የህወሀት ኩባንያ የሖነው ጉና የንግድ ድርጅት ግንባር ቀደም ቡና ላኪ ድርጅት እንዲሆን ካስቻሉ እና በርካታ ታዋቂ ነጋዴዎች ከቡና ንግድ እንዲወጡ ካደረጉ በሁዋላ መልቀቃቸውን ተችዎቻቸው ይናገራሉ። በዚህ ጊዜ ሥራቸውን የለቀቁት ፤የኢት ዮጵያ ቡና በ ዓለም ገበያ በመውደቁና በዘርፉ የሚታይ ተስፋ በመጥፋቱ ነው ሲሉም ያክላሉ።
ዶ/ር ኢሌኒ የኢት ዮጵያ ምርት ድርጅት በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሚያዚያ 2008 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ላለፉት አራት አመታት ድርጅቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተዋል። ዶ/ር ኢሌኒ ከስራ መልቀቅ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ነው። እርሳቸው ድርጅቱን ከማማከር ውጭ ለሌላ የፖለቲካ ሹመት መታጨታቸውን እንደማያውቁ እየገለጡ ነው።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide