በሲዳማ ዞን ከፍተኛ የሆነ የዘር ግጭት ሊነሳ ይችላል በማለት የአካባቢው ሰው በስጋት ወድቋል

ሰኔ አስራ አራት ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የአዋሳ ዘጋቢዎች እንደገለጡት ትናንት በአለታ ጩኮ የተነሳውን ተቃውሞ ተክትሎ በዛሬው እለትም ከአዋሳ በ 10 ኪሜ ርቅት ላይ በምትገኘው ቱላ ከተማ ውስጥ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውንና መኪኖችን አግተው ለመስክ ስራ የሄዱ ሰራተኞች ስራ ሳይሰሩ እንዲመለሱ ማድረጋቸው ታወቋል።
ተማሪዎች በየመኪኖች ውስጥ እየገቡ የወላይታ ተወላጆችን እንዲወርዱ ሲጠይቁ እንደነበር የገለጠው ዘጋቢያችን ትናንት ማታ 2 የወላይታ ተወላጆች በአዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ተገድለው መገኘታቸው ውጥረቱን አባብሶታል ብሎአል። በአዋሳ ከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ ሱቆች ግጭት ይነሳል በሚል መዘጋታቸውን ዘጋቢአችን ገልጧል። የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት በአዋሳና አካባቢዋ መስፈራቸውም ታውቋል። “አዋሳ ለወላይታ ተሽጣለች፣” አዋሳን እናድን፣ ለተቃውሞ ሰልፍ ውጡ” የሚሉ በራሪ ወረቀቶች እየተበተኑ ነው።
አዋሳ ለወላይታ ተሽጣለች የተባለው ምናልባትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውለድ ቦታ ጋር ሳይያዝ እንደማይቀር ነው ዘጋቢያችን የጠቆመው። ትናንት በአለታ ጩኮ በተነሳው ተቃውሞ 4 ሰዎች መገደላቸውን ፣ በዛሬው እለትም ሱቆች ፣ ትምህርት ቤትና መስሪያ ቤቶች ተዘግተው መዋላቸውን ዘጋቢአችን አክሎ ገልጧል።
በቅርቡ በፌደራል መንግስትና በሲዳማ ዞን ባለስልጣናት መካከል የተካሄደው ውይይት ያለውጤት መበተኑን መግለጣችን ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide