የእነ አቶ አንዱአለም አራጌ የፍርድ ውሳኔ ተራዘመ

ሰኔ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በእነ አቶ አንዱአለም አራጌ የክስ መዝገብ በአሸባሪነት ወንጀል ከ10 ወራት በፊት ከተከሰሱት 24 የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላት ፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት 8 ተከሳሾች ዛሬ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስማት በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቢቀርቡም በድጋሜ ቀጥሮ ወደ እስር ቤት እንዲመለሱ ተደርጓል።

ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰአት ከ35 ደቂቃ ላይ በችሎቱ የተሰየሙት  የመሀል ዳኛው እንዳሻው አዳነ፣ የቀኝ ዳኛው ሙሉጌታ ኪዳኔና የግራ ዳኛው ሁሴን ይመር የቅጣት ውሳኔውን ለሰኔ 20 ቀን 2004 ዓም ጧት አስተላልፈዋል።

ዳኛ ሁሴን ይመር በንባብ እንደገለጡት ዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት የግራ ቀኙን ክርክር መርምረን ስላልረጨረስን ውሳኔው ለዛሬ አልደረሰልንም ስለዚህም ለዛሬ ሳምንት  ተላልፎአል ብለዋል።

የታሳሪዎች ቤተሰቦች፣ የፓርቲ አመራሮችና አባሎች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የአሜሪካውን አምባሳደር ጨምሮ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ከጣቱ 2 ሰአት ከ 30 ጀምሮ ሶስተኛ ወንጀል ችሎት አዳራሽ ተገኝተው ነበር። የችሎት ታዳሚ በመብዛቱ ችሎቱ ክ 3ኛ ወደ 1ኛ ችሎት አዳራሽ ተዘዋውሯል ይሁን እንጅ ችሎቱ በግቢው ያለውን ሰው ለማስተናገድ ባመለቻሉ ሰዎች ለመግባት ሲጋፉ ታይተዋል። አጠቃላይ ሁኔታው ያናደዳቸው አንድ ግለሰብ በፍርድ ቤቱ ዋና በር ላይ ቆመው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ዳኞችን ” ለጥቅም የተገዛችሁ፣ ስብእና የሌላችሁ ሌቦች፣ ሌባ መንግስት እያሉ “በመጮሀቸው ፖሊሶች አስረዋቸዋል።

ከችሎቱ በሁዋላ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ የህግ ሰው የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላትና ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ ላይ ከቀድሞዎቹ የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች የተለየ ይፈረድባቸዋል ብለው እንደማይገምቱ ተናግረዋል። የህግ ባለሙያው ይህ ፍትህ ሳይሆን ፖለቲካ ነው ሲሉ አክለዋል።

ከጧቱ ሶስት ሰአት ተኩል ላይ እስረኞቹ በሽፍን መኪና እጆቻቸውን ለሁለት ለሁለት በካቴና ታስረው በጀርባ በር ወደ ችሎት የገቡ ሲሆን ፣ ቀይ ከረባትና ሱፍ ልብስ የለበሰው አንዱአለም አራጌ ከሳ ብሎ ና ጠቁሮ መታየቱን፣ እስክንድር ነጋ ከሳ ቢልም ጠንክሮና ተነቃቅቶ ታይቷል ሲል ዘጋቢያችን ገልጧል።

የግፍ እስረኞቹ የአረቡን አብዮት ተከትሎ መታሰራቸው ይታወቃል። የእነ አቶ አንዱአለም አራጌ እና የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መታሰር በኢትዮጰያ ውስጥ ያለውን የለውጥ ስሜት ሊቀይረው አልቻለም። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች አሁንም በአረቡ አለም የተካሄደውን አይነት ለውጥ በኢትዮጵያ ለማምጣት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአማራ ክልል በርካታ ወጣቶች በአካባቢያቸው የተለያ  እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች ያሳያሉ። ሁኔታው እያስደነገጠው የመጣው መንግስት ከሳምንት በፊት 5 የሰሜን ጎንደር እንዲሁም 1 የምእራብ ጎጃም ወጣትን ወደ አዲስ አበባ ማእከላዊ እስር ቤት በመውሰድ አስሯል።

በዛሬው ችሎት ላይ ወጣቶች ያሳዩት የነበረው የቁጭት መንፈስ፣ የእነ አንዱአለም እና እስክንድር መታሰር በወጣቱ ላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አለማስከተሉን የሚያሳይ ነው በማለት ዘጋቢያችን ዘገባውን አጠቃሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide