ሚያዚያ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሶስቱ የምስራቅ ዩክሬን ግዛቶች የተነሳው አመጽ እንደቀጠ ሲሆን የዩክሬን መንግስት አመጹ ካልቆመ በ48 ሰአታት ውስጥ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል፡
ሉሃንስ፣ ዶኔትስክ እና ካርኪቭ በተባሉት የዩክሬን ግዛቶች የሚኖሩ አብዛኞቹ ሩሲያውያን ፣ ከሩሲያ ጋር መቀላቀልን ወይም ነጻ የሆነ ግዛት የመመስረት ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት ቁልፍ የሚባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ይዘዋል።
ሩሲያ በክርሚያ እንዳደረገችው ሁሉ በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የምትገባ ከሆነ ኔቶ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ተጨማሪ እርምጃ በሩሲያ ላይ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።
ሩሲያ ማስጠንቀቂያውን ወደ ጎን በመተው ሰራዊቷን ወደ ድንበር እያስጠጋች መሆኑ ታውቋል።
የዩክሬን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ የሃይል እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ የሩሲያ መንግስት ጣልቃ ለመግባት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ተንታኞች ይናገራሉ።
የምስራቅ አውሮፓ አገሮች በበኩላቸው በሩሲያ ላይ ኔቶ ጠንካራ እርምጃ ካልወሰደ፣ ሩሲያ በመስፋፋት ፖሊሲዋ ቀድሞ ግዛቶቹዋን መልሳ ለመያዝ ወደ ሁዋላ አትልም ስትል እያስጠነቀቁ ነው።