የመረጃና ደህንነት አገልግሎት አወዛጋቢ አዋጅ ሥራ ላይ ዋለ

መጋቢት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ዓመት መጨረሻ በአዲስ መልክ በአዋጅ የተቋቋመውና ዜጎች መረጃ እንዲሰጡ የሚያስገደድደው ብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት አዲሱን አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በ1987 ዓ.ም የደህንነት የኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን በሚል ስያሜ ተቋቁሞ በስራ ላይ የነበረው ይህው ተቋም የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት እንዲችል በሚል ባለፈው ዓመት አዲስ የማሻሻያ ረቂቅ ለፓርላማው ቀርቦ መጽደቁ ይታወሳል፡፡

አዲሱ አዋጅ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ በመረጃና ደህንነት ዙሪያ የስጋቶች ምንጭ እና የመከላከያ ስርዓትና አሰራር እየተለዋወጠ በመምጣቱ፣በአገር ውስጥ የጸረ ሽብርተኝነት እና የበረራ ደህንነት የማስጠበቅ የመረጃና ደህንነት ተጨማሪ ሃላፊነቶች በአገልግሎቱ ስልጣንና ሃላፊነት ውስጥ እንዲካተቱ እንደተደረገ ያገኘነው መረጃ ይጠቅሳል፡፡

በዚህ አዋጅ መሠረት በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ ሌላ የመረጃና ደህንነነት መ/ቤት ማቋቋም የተከለከለ ሲሆን የመ/ቤቱ ገቢና ወጪ ሂሳብ ይፋዊ በሆነ መንገድ በኦዲተር እንዳይመረመርና ሂሳብ ነክ ጉዳዮች ለጠ/ሚኒስትሩ ብቻ ሪፖርት እንደሚያደርግ ደንግጓል፡፡

ለመ/ቤቱ ከውጪ ተገዝተው የሚገቡና በተለያየ ምክንያት ለስራ ተብለው የሚወጡ ዕቃዎች ጉምሩክ ሳያያቸው እንዲወጡና እንዲገቡ የተደነገገ ሲሆን የደህንነት ሠራተኞች ሃብት ምዝገባ በጸረ ሙስና ኮምሽን ሳይሆን በተቋሙ እንደሚከናወን ይገልጻል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተጨማሪም ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት መረጃ በሚጠየቁበት ጊዜ ትብብር ያለማድረግ ሁኔታ ለሥራው እንቅፋት መሆኑን በመጥቀስ መረጃ መስጠት ግዴታ እንዲሆን በአዋጁ ደንግጓል፡፡ ይህን አዋጅ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል ተቋሙ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በተለይ ከመጪው ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሕግና ስርዓትን ለማስከበር በሚል ዜጎች መረጃ ስጡ እየተባሉ ለእንግልትና ለእስር እንዳይዳረጉ ከወዲሁ ስጋት ፈጥሮአል፡፡