አቶ ሃይለማርያም ወ/ሮ አስቴር ማሞን ሾሙ

መጋቢት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ዛሬ ፓርላማ በድንገት ተገኝተው የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩትን ወ/ሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር እንዲሆኑ ያቀረቡትን ሹመት ፓርላማው ተቀብሎ አጽድቋል፡፡

የኦህዴድ ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዚደንት ከነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ሞት በኃላ ኦህዴድ ባደረገው የሥልጣን ሽግሽግ አቶ ሙክታር ከድር ከምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ተነስተው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ ወ/ሮ አስቴር ማሞም በአቶ ሙክታር እግር ተተክተዋል፡፡

ወ/ሮ አስቴር ማሞ በጰጉሜ ወር 2002 ዓ.ም በተካሄደው የኦህዴድ ጉባዔ ከድርጅቱ ሥራ አስፈጻ ኮምቴ አባልነት አሰንባቷቸው የነበረ ሲሆን  በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም የተካሄደው የኦህዴድ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ግርማ ብሩን ከፓርቲው ሥራ አስፈጻሚነት ሲያሰናብት ወ/ሮ አስቴር  ተመልሰው ለመመመረጥ ችለዋል፡፡ የአቶ አለማየሁ ሞት ተከትሎ በቅርቡ ፓርቲው ባደረገው ሽግሽግ ከኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው ተሹመዋል።

ወ/ሮ አስቴር በህወሃቶች ዘንድ እንደታማኝ ይታያሉ።