ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ያለተፎካካሪ ሥልጣኑን በኃይል የተቆጣጠረውን ኢህአዴግ በማስወገድ የሕዝብ ሥልጣን ባለቤትነትን ለማምጣት ብቸኛው መፍትሔ በፅናትና በቆራጥነት መታገል ብቻ መሆኑ ተገለፀ።
የ33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ ትላንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ሀገራችን ከገባችበት ፈተናና ሕዝቡ ከሚቀበለው ሥቃይ ልናላቅቀው የምንችለው ከያዘን የፍርሃት ቆፈን ተላቀን ባንድነት በመቆም ቀኑ የደረሰውን አምባገነን ሥርዓት ወደተመኘው መቃብር ለመሸኘት በጽናት መታገል ብቻ ነው ብሏል።
የ33ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር ሆነው ለሚያደርጉት ትግል በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን፣ አቅማቸውንና ጊዜያቸውን አስተባብረው ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ፓርቲዎቹ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ድምፁ ለታፈነውና የሰቆቃ ሕይወት ለሚገፋው ወገናቸው ድምፅ በመሆን የትግሉ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን በመኖርና ባለመኖር መካከል በጣለበት በአሁኑ ወቅት መንግሥት “ይህ የሆነው የኢኮኖሚው ዕድገታችን ፍጥነት ነው፣ ጤፍ የሚበላው ሰው በመጨመሩ ነው” እያለ በሕዝቡ ላይ ያላግጣል ያለው መግለጫ፤ ከዚህ ንቀት የተሞላበት አምባገነናዊ ሥርዓት ለመገላገል ብቸኛው መፍትሔ የተደራጀ ትግል ማድረግ ነው ብሏል።
በ33ቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኅብረት የወጣው ይህ መግለጫ ለዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብና ሃገራት፤ በሀገራችን ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደልና ሥቃይ በመረዳት ከሕዝብና ከሕዝቡ ትግል ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።