ኢትዮጵያ በሚመጣው ዓመት የኤሌክትሪክ እጥረት ያጋጥማታል

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የ200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንደሚያጋጥማት ጥናቶች አመለከቱ። ሀገሪቱ ይህንን ችግር ለመወጣት ባለፉት ዓመታት በወር 100 ሚሊዮን ብር ለጄኔሬተሮች ወጪ ስታደርግ ቆይታለች አሁንም በማውጣት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ያካሄደውን ጥናት ጠቅሶ ካፒታል ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ሀገሪቱ በሚቀጥለው ዓመት የሚያጋጥማት የ200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ኢኮኖሚውን ክፉኛ ሳይጎዳው የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰድ ይገባቸዋል ይላል።

ባለፉት ሁለት አመታት የሚያጋጥሙ የኤሌክትሪክ እጥረቶችን ለመቋቋም የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል የሚለው ጥናት በወር100 ሚሊዮን ብር የሚያስወጡ 45 የናፍጣ ጄኔሬተሮችም በተለያዩ ቦታዎች መተከላቸውን ገልጧል።

የኮርፖሬሽኑን ምንጮች የጠቀሰው ካፒታል ጋዜጣ በሀገሪቱ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማሉ ካሉ በኋላ በተለይ በቅርቡ ካንዱ ኢንዱስትሪ ብቻ  የቀረበ የ300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ጥያቄ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ሊያቀርብለት አይችልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገሮች ጅቡቲና ሱዳን እንደሚልክ ሲናገር ቆይቶ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ማስተናገድ አለመቻሉ ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ሆኗል ።