የፌደራል ፖሊስ የግዥ አፈፃፀም ሥርዓት ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን የጸረ ሙስና ኮምሽን በጥናት አረጋገጠ

ሐምሌ ፰( ስምንት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን በቅርቡ ባካሄደው የአሰራር ሥርዓት ጥናት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የግዥ አፈፃፀም ለሙስና እና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ነው ብሎአል፡፡

በፖሊስ ኮምሽኑ የተጠና የጠቀሜታ ዝርዝር /ስፔስፊኬሽን/ አዘገጃጀት አሰራር አለመኖር፣ ግዥዎችን በዕቅድና
በፕሮግራም አለመፈፀም፣ በጀት መኖሩ ሳይረጋገጥ የግዥ ሂደቶችንማከናወን፣ በግዥ መመሪያው ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ግዥ መፈፀም እና የጨረታ ኮሚቴው ከግዥ መመሪያውን ተከትሎ አለመሥራት ዋና ዋና ጉድለቶች መሆናቸውን ኮምሽኑ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡

የፌደራል መንግሥት የግዥ አፈፃፀም ሥርዓት መመሪያ የጠቀሜታ ዝርዝር /ስፔስፊኬሽን/ በተጠቃሚዎች ዝርዝር ላይ የተመሠረተ ሆኖ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን የሚፈለገውን ለማሟላት ያላቸውን ተፈጥሮ፣ የሚያስገኙትን ውጤት፣ ለመሥሪያ ቤቱ የሚያስገኙትን ጠቀሜታ፣ የአሠራር ባሕሪያቸውንና የታቀደላቸውን ሥራ ለማከናወን ያላቸውን የብቃት ደረጃ የሚያካትት ዝርዝር መግለጫ መዘጋጀት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ በፌደራል ፖሊስ መሥሪያ ቤት የሚዘጋጁት አንዳንድ የጠቀሜታ ዝርዝሮች  የሚገዙትን ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች በግልጽ የሚያሳዩ ባለመሆናቸው የግዥ ውሳኔዎች ወደአልተፈለጉ አቅጣጫዎች እንዲያጋድሉ በማድረግ የአሠራር ክፍተቶች ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጥናቱ ያሳያል፡፡

በዕቅድና በፕሮግራም ግዥዎችን አለመፈፀም ሌላው በኮሚሽኑ የታየ ለሙስና እና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጥ አሰራር ነው ተብሎአል፡፡ ያለ ፕሮግራምና ዕቅድ አስቸኳይ እየተባሉ የሚፈፀሙ ግዥዎች በአይነትም ሆነ በመጠን ከፍተኛ በመሆናቸው ኮሚሽኑን ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳርጉ፣  የጥድፊያ ግዥ አሠራርለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተመቻቸ ከማድረጉም በላይ የተገዙት ዕቃዎች ለረዥም ጊዜ ቦታ አጣበው ያለ አገልግሎት እንዲከማቹ፣ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑና ለብልሽት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል ብሏል ሪፖርቱ።

የተጠናከረ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ አለመኖሩ በጥናቱ የታየ ችግር ነው፡፡የውስጥ ኦዲት በግዥ ኮሚቴ በታዛቢነት የሚሳተፍ ካለመሆኑም በላይ በተሟላ መልኩ ሥራውን ኦዲት የማያደርግበመሆኑበሥራ
አጋጣሚ የሚከሰቱትን ክፍተቶች በማውጣት ለማኔጅመንቱ አጋዥ ሪፖርት በማቅረብ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ የሚያስችልበት ሁኔታ ጉልህ ሆኖ  አለመታየቱም ተጠቅሷል። በቀጣይ የኮሚሽኑ የውስጥ ኦዲት በጨረታ ኮሚቴ ውስጥ በታዛቢነት የሚሳተፍበትና በየወቅቱ የሥራ ሪፖርት ለማኔጅመንቱ የሚያቀርብበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጥናቱ አክሎ ጠቁሟል፡፡