የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች አመጽ እንደቀጠለ ነው።

ሐምሌ ፰( ስምንት )ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ከጎናቸው እንዲቆም በመጠየቅ ትናንት በአመታዊ የሥላሴ ክብረ በዓል ላይ  መፈክሮችን ሲያሰሙ ውለዋል።

ተማሪዎቹ ሲያሰሙዋቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል፦የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን መዝጋት ታሪክን ማጥፋት/ማበላሸት ነው!፣የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ችግራችንን ይመልከት!፣ሙስናንና ኑፋቄን የሚያደቅ ክንድ አለን!የምንማረው በምእመናን ብር ነው፡፡ ሌቦች ሆይ፣ እጃችኹ ይሰብሰብ! “የሚሉት ይገኝበታል።

እንዲሁም፦”ልጆቹን የማይጠይቅ አባት አለን?”በማለት በጥያቄ መልክ ድምፃቸውን ሲያስተጋቡ የነበሩት ተማሪዎቹ፤

“ችግራችንን የሚሰማንና መፍትሔ የሚሰጠን አባት ዐጣን!፣የቅ/ሲኖዶሱ አባላት ትኩረት ይስጡን!፣ሙስናን በቃል ሳይኾን በተግባር እንዋጋ! ተማሪዎች ሙስናን በመዋጋታቸው ሊበረታታቱ እንጂ ሊባረሩ አይገባም!”ብለዋል።

“ከአየህጉረ ስብከቱ ቤተ ክርስቲያንን አምነን ወጥተን ለረኀብ ተጋለጥን፡፡”ያሉት ተማሪዎቹ ኮሌጁ በመዘጋቱ  ምግብ ከተመገቡ ሰባተኛ ቀናቸውን እንዳስቆጠሩ ተናገረዋል።

“አቤቱ የኾነብንን አስብ፡፡” የሚለውንና በመጽሀፍ ቅዱስ የሚገኘውን የኤርምያስ ሰቆቃ በጋራ ሲሉ የተደመጡት የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹ፤ኮሌጁን የሚዘጋውና የሚከፈተው ሲኖዶስ ነው ብለዋል።
የተቃውሞ መፈክራቸውን በመቀጠል፦”“ኮሌጁ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የግለሰቦች አይደለም!፣እውነትን- ሙስና አይደለም መቃብር አያሸንፈውም!”ሲሉ የተደመጡት ተማሪዎቹ፤እየሞትንና እየተራብንም ቢሆን  ሙስናንና ዘረኝነትን እንቃወማለን!”ብለዋል።
ይህ  በእንዲህ እንዳለ፡ሐራ ተዋሕዶ የተባለው ድረ ገጽ እንደዘገበው ተማሪዎቹ፡በነገው ዕለት በመንበረ ፓትርያሪኩ በሚያካሂዱት ከፍተኛ የተቃውሞ ትዕይንት ምእመኑ ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኮሌጁ ተማሪዎች ዛሬ ባወጡት መግለጫ-ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ከመሳለምና ገንዘብ ከመስጠት/ከመመጽወት ባሻገር ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ጉዳይ በመጠየቅ ቀጥተኛ ተሳታፊ መኾን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

 

ደቀ መዛሙርቱ ማሳሰቢያውን ያስተላለፉት፣ በዛሬው የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል አጋጣሚ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለተገኘው ምእመን የኮሌጁ አስተዳደር በትምህርት አመራሩና በአካዳሚያዊ መብቶቻቸው ላይ ስለሚፈጸመው በደል በገለጹበት ወቅት ነው፡፡

 

አንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ÷ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የመምሪያ ሓላፊዎችን፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንን፣ ተመራማሪዎችን፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች በከፍተኛ ሓላፊነት ላይ የሚገኙ ቀደምት ምሩቃንን ያፈራ መኾኑን ደቀ መዛሙርቱ ለምእመናኑ አስታውሰዋል፡፡

 

ኮሌጁ አገልግሎቱን የሚያከናውነው ‹‹በእናንተው ገንዘብ ነው›› ያሉት ደቀ መዛሙርቱ፣ ‹‹የምእመኑ ሥራ ገንዘብ መስጠት ብቻ አይኹን፤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችኹ ጠይቁ፤ ይህ ኮሌጅ የሕዝብ ነው፤ ነገር ግን የገጠር አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ፣ መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተው ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ቅርጫ ሥጋ ሊከፋፍሏት ባሰፈሰፉበት ወቅት በግለሰቦች እየተዘጋ ነው›› በማለት ከአስተዳደሩ ጋራ ሙስናን፣ ኑፋቄንና ብልሹ አሠራርን በመቃወም የገቡበትን ውዝግብ በሰፊው አብራርተዋል፡፡

 

ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ከዐሥር ጊዜያት በላይ በጋራና በተወካዮቻቸው በመመላለስ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ መቆየታቸውን የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ በጥበቃ እየተገፈተሩ ያለውጤት ከመንገላታት በቀር ያገኙት ነገር ባለመኖሩ ምእመኑን፣ ‹‹በየብሔረሰቡ በተለያየ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያንን የምናገለግል ልጆቻችኹ ነን፤ ሙሰኞቹ ኀያላን ናቸውና ርዱን! ነገ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሁለት ሰዓት በምናደርገው እንቅስቃሴ አብራችኹን ቁሙ!!›› ሲሉ በከፍተኛ አጽንዖት ተማፅነዋል።

 

በሌላ በኩል አቡነ ጢሞቴዎስ ደቀ መዛሙርቱን በፖሊቲከኝነት መወንጀል ቢጀምሩም፤የተማሪዎች መማክርት በበኩሉ፡የኮሌጁን አስተዳደር በሕግ ለመጠየቅ እየተዘጋጀ ነው።

ተማሪዎቹ በዛሬው ተቃውሟቸው “ጢሞቴዎስ ሆይ አደራህን ጠብቅ!” የሚለውን የመጽሀፍ ቃል በማሰማት ለ አቡነ ጤሞቴዎስ መልእክት ሲያስተላልፉ ተሰምተዋል።