የፌደራል መንግስት የባህርዳር ጊዮን ሆቴል በአስቸኳይ እንዲመለስ ትእዛዝ መስጠቱ ታወቀ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለኢሳት እንደገለጹት የፌደራሉ መንግስት ለአማራ ክልል ኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ባስተላለፈው ተእዛዝ ፣ የሆቴሉ ኪራይ ተስልቶ አስፈላጊው እርክክብ እንዲደረግ አዟል። የክልሉ የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲም ለባለሀብቶቹ በጻፈው ደብዳቤ ሆቴሉን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2005 ዓም ፣ አስፈላጊውን ኪራይ ከፍለው እንዲያስረክቡ ማዘዙ ታውቋል።

ባለሀብቶቹ ለወደፊቱ የመረጡት ቦታ ላይ መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው ለማወቅ ተችሎአል።

የዛሬ 21 አመት ህወሀት/ ኢህአዴግ አሸንፎ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት ለህወሀት ወኪል በመሆን  ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው የሚታወቁት በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ዘመድ አቶ ወልዱ፣  የህዝብ  ንብረት የሆነውን ጊዮን ሄቴልን በ5 ሺ ብር ኪራይ እንዲሰሩበት በገጸ በረከት እንደተሰጣቸው መዘገቡ ይታወሳል።

አቶ ወልዱ በልጃቸው በአቶ ብስራት ወልዱ ዋና አስተዳዳሪነት ሆቴሉን ሲሰሩበት እና ከፍተኛ ገቢ ሲሰበስቡበት ከቆዩ በሁዋላ፣ ህዝቡ ጊዮን ሆቴልን የሚያክል በስፋቱና በጥራቱ ተወዳዳሪ የሌለውን ሆቴል እንዴት መንግስት በ5 ሺ ብር ያከራያል? በማለት ተቃውሞ ሲያሰማ መቆየቱን ተከትሎ፣ የፌደራል የኪራይ ቤቶች ድርጅት የክልሉ መንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሆቴሉን እንዲረከብ ለአማራ ክልል ቤቶች አስተዳዳር አምና ደብዳቤ መጻፉን መዘገባችን ይታወሳል። ይሁን እንጅ  አቶ በረከት እና በ አቶ አዲሱ ጣልቃ ገብነት የሆቴሉ ባለቤቶች ሆቴሉን እንደያዙ እንዲቆዩ ተደርጎ ነበር።

ልዩ ትእዛዝ ካልመጣ በስተቀር የሆቴሉ ርክክብ እንደሚፈጸም ምንጮቻችን ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የሆቴሉን ባለቤቶች ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።