የመንግስት ባለስልጣናት በበጎ ነገር ምሳሌ የሚሆነን መሪ አጥተናል አሉ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዛሬ በባህርዳር ከተማ በኩሪፍቱ መናፈሻ በከፍተኛ ጥበቃ በተካሄደው የፌደራል እና የክልሎች የሰቪል ሰርቪስ የቢሮ አመራሮች ግምገማ  ተሰብሳቢዎቹ ” በበጎ የምናነሳው ምሳሌ የሚሆን መሪ አጥተናል ፣ ኢህአዴግ እና  ሲቪል ሰርቪሱ ሆድና ጀርባ ሆነዋል በማለት” ተናግረዋል።

በመንግስት የሚወጡ መመሪያዎች ያለሰራተኛው ፈቃድ ተግባራዊ እንደሚሆኑ የገለጹት ተሰብሳቢዎች፣ሲቪል ሰርቪሲ የፓርቲ አገልጋይ በመሆኑ ትክክለኛ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም በማለት ተናግረዋል። ተገዶ አባል እንዲሆን የሚጠየቀው ሰራተኛ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ካልሆነ የባላንስ ስኮር ካርድ በሚል ሰበብ ውጤት ይቀነስበታል በማለት ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል። አባልነትን ሰራተኛው ላለመባረር መሸሸጊያ እያደረገው ነው በማለት ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ በልስቲ በዛሬው ውይይት በሲቪል ሰርቪስ ድክመቶችና ጥንካሬዎች ዙሪያ እንዲሁም የልማት ሰራዊትን በመገንባት ዙሪያ መወያየታቸውን ለኢሳት ተናግረዋል።

ስብሰባውን የመሩት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ  ዶ/ር  ምስራቅ ናቸው።