መንግስት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስቦ በየወረዳው ፖሊስ ጣቢያ አጎረ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአፍሪካ ህብረት 50ኛ አመት ክብረ በአል ጋር በተያያዘ የመንግስትን ምስል ያበላሻሉ የተባሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች በፌደራልና በአዲስ አበባ ፖሊሶች እየተያዙ በየጣቢያው እንዲታጎሩ ተደርገዋል።

ትናንት ፖሊሶች ሲቪል በመልበስ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ያፈሱ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በልመና የሚተዳደሩትን  አፍሰዋል።

መንግስት አለማቀፍ ስብሰባዎች ሲኖሩ ወይም የኢህአዴግ በአላት ሲከበሩ የመንግስትን መልካም ገጽታ ያበላሻሉ የሚባሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እየታፈሱ በፖሊስ ጣቢያዎች እንዲታጎሩ ይደረጋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባን ፖሊስ ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም ሀላፊዎችን ለማግኘት አልቻልንም።