አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አፈና ቀጥሏል አለ

ግንቦት ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለሰብአዊ መብቶች መከበር በመሟገት አለማቀፍ እውቅና ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገው የዚህ አመት ሪፖርት መንግስት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማፈኑን፣ የነጻውን ሚዲያ ፣ የፖለቲካ ድርጅቶችንና የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴዎችን መግታቱን ገልጿል።

“ሰላማዊ ተቃውሞ ማድረግ ተከልክሏል፣ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰዎችን ማሰር ፣ ማሰቃየት እና በእስር ቤቶች ውስጥ ሰቆቃዎችን መፈጸም ቀጥሏል” ያለው አምነስቲ “ዜጎችን በሀይል ከመኖሪያ ቀያቸው የማፈናቀሉ  እንቅስቃሴም” መጨመሩን አመልክቷል።

በርካታ ጋዜጠኞች መንግስትን በመተቸታቸው፣ የፖሊሲ ማሻሻል እና ለውጥ እንዲደረግ በመጠየቃቸው በሽብርተኝነት ተከሰው የብዙ አመታት እስር ተፈርዶባቸዋል ። በመንግስት በኩል ለፍርድ ቤት የሚቀርቡት ማስረጃዎች ሲታዩ ተካሳሾች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የመሰብሰብ መብታቸውን ተጠቅመው ያደረጉት እንጅ በሽብርተኝነት የሚያስከስሳቸው አለመሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።

ድርጅቱ በፍትህ ጋዜጣ ፣ በሙስሊም የድምጻችን ይሰማ መሪዎች እና ደጋፊዎች ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህገወጥ እርምጃም ተንትኖአል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች በዱላ፣ በቦክስ፣ በጥፊ እንደሚመቱ፣ እጃቸው  ከግድግዳ ጋር ወይም ከጣራ ላይ

ታስሮ እንደሚደበደቡ፣ እንቅልፍ እንዳያገኙ፣ ለብቻቸው እንዲታሰሩ፣ በኤልክትሪክ እንዲጠበሱ፣ ውሀ ውስጥ እንዲዘፈቁ፣ በብልታቸው ላይ ከባድ እቃ እንደሚንጠለጠልባቸው፣ ተገደው የራሳቸው ያልሆነውን ቃል የራሳቸው እንደሆነ አድርገው እንዲፈርሙ እንዲሁም አንዱ እስረኛ ሌላውን እንዲደበድብ እንደሚደርግ አምነስቲ በሪፖርቱ ጠቅሷል።

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንደሚገድሉ፣ በአፋር፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊ እና በሌሎችም ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በዋቢነት አንስቷል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በደቡብ አካባቢዎችም ዜጎች በሰፋራ ስም እንደሚፈናቀሉ አምነስቲ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ላይ ጠቅሷል።

በጉዳዩ ዙሪያ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ሉሲ ፍሪማን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ መብቶችን መጣስ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የዘንድሮውም ሪፖርት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ችግሮች እየተባባሱ መሄዳቸውን የሚያመለክት እንጅ መሻሻል እንዳልታየበት ሚስ ፍሪማን ገልጸዋል

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ሰብአዊ መብት በአፍሪካ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደረጃ እያቀረበ እንደሚገኝ ሚስ ፍሪማን ገልጸዋል