ኀዳር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጎንደር ከተማ የሚገኘውና ባሕታ በመባል የሚጠራው ማረሚያ ቤት ግቢ ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ የሆነ አደጋ የደረሰበት ሲሆን ቁጥራቸው ከ30 እስከ 50 የሚሆኑ ታራሚዎች መገደላቸውንና ከ300 እስከ 500 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ደግሞ አምልጠው ከሕዝቡ ጋር ሲቀላቀሉ ከ100 በላይ የሚሆኑት እስረኞች በእሳት ቃጠሎው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የፌዴራል ፖሊሶች ከውስጥና ከውጭ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ታራሚዎችን መገደላቸውና መውጫ አጥተው በእሳት ቃጠሎ እያረሩና እየነደዱ መሆኑን የዓይን እማኞች ይናገራሉ። የፌደራል ልዩ ኃይልና የወሕኒ ቤቱ ፖሊሶች ቃጠሎውን ከማጥፋት ይልቅ በእስረኞቹና በነዋሪው ላይ በኃይል አሰቃቂ እርምጃዎችን በመውሰድ አደጋውን የከፋ አድርገውታል።
ሕዝቡ አንፈልጋችሁም ለቃችሁ ውጡልን ልጆቻችንን አትግደሉ በማለት ቁጣውን እየገለጸ ነው።ሞት ለወያኔ! ሞት ለብአዴን! የሚሉ መፈክሮች በማንገብ ሕዝቡ ደጀንነቱን አሳይቷል። ጎንደር የጦር ቀጠና ውስጥ ስትሆን ሕዝቡ የእስረኞቹን ሕይወት ለመታደግ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈሉን ቀጥሏል።የታራሚዎቹ ቤተሰቦች እና የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ በሆነ ሃዘን ውስጥ ከመርውደቃቸው በተጨማሪ የጉዳቱን መጠን በውል ማወቅ አልተቻለም። ተጨማሪ ጦር ከአዘዞና ከልዩ ልዩ ቦታዎች በመኪና ተጭኖ እየመጣ ነው፡፡እስረኞች ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በእሳት ይጋያሉ፣ ይገደላሉ፣ ታስረው እየተደበደቡ ከፍተኛ ስቃይና ግፍ እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ።እስከ አሁን ድረስ የክልሉ መንግስትና የፌደራል መንግስት ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጡም።