የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች ከፍተኛ ክስ ቀረበባቸው፡፡

ኀዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ሳሞንት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞችና መምህራን ለትምህርት ሚኒስቴሩ ሽፈራው ሽጉጤ ሰብስበው እንዲያነጋግሯቸው በፃፉት ደብዳቤ መሰረት ሚኒሰቴሩ በዩኒቨርሲቲው ግቢ በመገኘትና ስብሰባ በማዘጋጀት ያነጋገሯቸው ሲሆን ፣ በስብሰባው የተገኙት ታዳሚዎች ተራ በተራ እየተነሱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በሆኑት ዶ/ር ስለሺ ቆሬ ላይ 29 የሚደርሱ በማስረጃ የተደገፉ የተቃውሞ ክሶችን አሰምተዋል፡፡
በፕሬዝዳንቱ የግል የባንክ አካውንት ከ4 ሚሊየን ብር በላይ መገኘቱና በአዲስ አበባ፡ በሀዋሳና በዲላ የመኖሪያ ቤት ያላቸው መሆኑን፣ በዩኒቨርሲቲው በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ካለው የከተማዋ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በተያያዘ ሙስና ሰርተዋል የሚልና ከ10 አመት በፊት ጡረታ የወጡ የፕሬዝዳንቱ አባት በዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል የግዢ ክፍል ተቀጥረው መገኘታቸውና ዘመዶቹን ጨምሮ ሌሎች 200 የሚጠጉ ሰራተኞች ከዩኒቨርሲቲው የሰው ሃይል መመሪያ ውጭ ተቀጥረው መገኘታቸው፡ የልማት ፖስተር ( ታፔላ) ለማዘጋጀት በሚል ከፍተኛ ገንዘብ እንዲወጣ በማድረግ እንዲሁም ሴት ሰራተኞች ላይ የወሲብ ጥቃት በተለይም አንዲት የዩኒቨርሲቲው መምህር ባለትዳር ሴትን ለማማገጥ የተለያዩ ፅሁፎችን ወደ ስልኳ እየላኩ ማስቸገራቸውን የሚመለከቱ ክሶች በፕሬዚዳንቱ ላይ ቀርበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ፕሬዝዳንቱ የሚሰጡት መልስ እንዳለ የጠየቁዋቸው ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ አዲስ አበባና ዲላ ቤት እንዳላቸው ያመኑ ሲሆን ሃዋሳ ግን ቤት የለኝም ብለዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹም “እንዴት በትምህርት ላይ የቆየ ሰው ይሄን ያህል ንብረት ይኖረዋል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሰብሳቢው ውሳኔውን በቅርብ ቀን እንደሚያሳውቁ ከገለጹ በሁዋላ፣ ፕሬዝዳንቱ ከስራ የተነሱ ሲሆን ለከፍተኛ ፍርድ ባለመቅረባቸውና ይህን አይነት ወንጀል በመንግስት ሚዲያ ሳይዘገብ በመቅረቱ መምህራንና ሰራተኞቹን ቅሬታ ተሰምቶዋቸዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው መምህራን ለስራ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩና በተደጋጋሚ ለሚያነሷቸው ከስራ ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች መልስ በማጣታቸውና አድሏዊ አሰራር በመኖሩ በብዛት ስራ እየለቀቁ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ ባለቤት አባት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ኢሳት ተጨባጭ ማስረጃዎችን የፋ ማድረጉ ይታወሳል።