በሃሮማያ ዩንቨርሲቲ የተማሪዎች አመጽ አሁንም አልበረደም

ኀዳር ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሃሮማያ ዩንቨርሲቲና በተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ የኦሮሚያ ተወላጆች የሆኑ ተማሪዎች አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አርሶአደሮችን ከቀያቸውና ከእርሻ ማሳቸው ላይ ያፈናቅላል በማለት ቁጣቸውን በሰላማዊ ተቃውሞ የገለጹ ቢሆንም መንግስት እንደተለመደው የኃይል እርምጃ ወስዷል። ተቃውሞ ለማፈን በተወሰዱ እርምጃዎች የፌደራል ልዩ ጦር በማሰማራት ግድያና አካላዊ ጥቃት ተፈጸሟል። በዚህም ሳቢያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች መገደላቸውንና ከ50 በላይ የሚሆኑት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።በአዳማ ዩንቨርሲቲ አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ተወደደም ተጠላም ማስተር ፕላኑ ስራ ላይ ይውላል ይተገበራል! እምቢ ያለውን ልክ እናስገባዋለን! በማለት አባይ ፀሃዬ ዛቻቸውን ከማሰማታቸው በተጨማሪ ማንም ተማሪ ከግቢው እንዳይወጣ ቤተሰብም ወደ ዩንቨርሲቲዎች እንዳይገባ ታግዷል።