የጌዲዮ ተፈናቃዮች ሁኔታ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2011) በጌዲዮ ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ በአካባቢው የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።

ከህክምና ቡድኑ አባላት አንዱ ለኢሳት እንደገለጹት በአካባቢው ካለው የምግብና የውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ በርካታ ተፈናቃዮች ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል።

ህጻናት ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ርብርብ ቢደረግም ሕጻናቱን ከህመም ለመታደግ አልተቻለም ሲሉ ይገልጻሉ።

በጌዲዮ ያለው የተፈናቃዮች ሁኔታ በቃላይ ከሚገለጸውና በወረቀት ከሚጻፈው በላይ ነው ይላሉ በአካባቢው የተሰማሩት የህክምና ባለሙያዎች።

ወደ አካባቢው የሚመጣውን እርዳታ ለተፈናቃዮቹ ለማድረስ ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግም ውጤት ግን ማምጣት አልተቻለም ይላሉ በአካባቢው ከተሰማሩት የህክምና ባለሙያዎች አንዱ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ።

በመፈናቀሉ በዋናነት ተጎጂ የሆኑ ህጻናት ለመታደግ የሚደረገው ርብርብም ቢሆን የታሰበውን ያህል ሊሄድ አልቻለም ይላሉ።

እንደ ህክምና ባለሙያው አባባል ህጻናቱ በተደጋጋሚ የሚጠቁት በተላላፊ በሽታዎች መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ።

ከዚህም ሌላ ይላሉ ባለሙያው አሁን ላይ በአካባቢው እየጣለ ያለው ዝናብ ሌላ አደጋ ደቅኗል ባይ ናቸው።

ተፈናቃዮቹ ያለምንም መጠለያ ሜዳ ላይ መውደቃቸውና በዛው መጠን ተላላፊ በሽታው የሚያስከትለው ጉዳት እየከፋ መምጣቱ ሁኔታዎቹን አስፈሪ አድርጓቸዋል ሲሉ ይገልጻሉ።

ጨለጨሌ በሚል በሚጠራውና 45 ሺ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ያሉበትን ቦታ እንደምሳሌ ያነሳሉ የህክምና ባለሙያው።

ለተፈናቃዮቹ የሚደርሰው በሶስት ቀን አንድ ጊዜ የሚደርሰው ምግብና በሰባት ቀን አንዴ ተሰፍሮ የሚሰጠውን ሁለት ሊትር የማይሞላ ውሃ በማሳያነት ያቀርባሉ።

እንደ ህክምና ባለሙያው አባባል በሕይወትና ሞት መካከል ላሉት ተፈናቃዮች አስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀ ችግሩን በቀላሉ ማቆም አይቻልም።