አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ለማ መገርሳ ተሾሙ

 (ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 9/2011)አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ለማ መገርሳ የውጭ ጉዳይና የሀገር መከላከያ ሚኒስትሮች ሆነው ተሾሙ።

የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በአቶ ለማ መገርሳ ምትክ ክልሉን እንዲመሩ ተሹመዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበለትን የሚኒስትሮች ሹመት አጽድቋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ  ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትር  ሆነው ተሹመዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነዋል።

በእጩዎቹ ሹመት ዙሪያም የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበው ነበር።

የምክር ቤቱ አባላት፣ሚኒስትሮች ሲቀየሩ ምክንያቱ አብሮ ለምን አይገለጽም?

አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ነበሩ ፤ ከክልል ለምን ተነስተው ወደዚህ መጡ የሚሉ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ጫላ ለሚ  በሰጡት ምላሽ በሚኒስትሮች ሹመቱ ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተቀነሰ እንደሌለ ነው የገለጹት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ወርቅነህ ለሌላ ስራ በመልቀቃቸው በምትካቸው መሾሙን በማስታወቅ።

የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኢንጂነር አይሻም በሙያቸው እንዲመደቡ ተደርጎ በምትካቸው አቶ ለማ መመደባቸውንም ገልፀዋል።

ሁለቱ እጩዎች ከክልል ርዕሰ መስተዳድርነት የተነሱትም በክልል ላይ ችግር ስላለባቸው ሳይሆን፥ በአሁን ወቅት ሃገሪቱ ላለችበት ለውጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ በመሆናቸውና የፌዴራል መንግስቱን የበለጠ ለማጠናከር ታስቦ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበለት የሚኒስትሮች ሹመት ላይ ከተወያየ በኋላ በአንድ ተቃውሞ፣ በአምስት ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጨፌ ኦሮሚያ ባካሄደው አራተኛ አስቸኳይ ስብሰባው  አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ሆነው በአቶ ለማ መገርሳ ምትክ  ተሹመዋል።

አቶ ሽመልስ ዛሬ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እስከሚሾሙ ድረስ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሀላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በተያያዘ ዜና አቶ አዲሱ አረጋ የኦዲፒ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል።