በአፋር ክልል ወጣቶችን ማዋከብ ተጠናክሮ ቀጥሏል

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2011)በአፋር ክልል ወጣቶችን የማዋከብና የማስፈራራት ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።

የአፋር የሰብአዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአስ አህመድ ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ከሆነ ወጣቶቹ በክልሉ ያሉት አሰራሮች ይቀየሩ በሚል በሰላማዊ መንገድ ለሚያቀርቡት ጥያቄ እየተሰጣቸው ያለው ምላሽ መሳደድ ሆኗል።

ዛሬ ላይ ይላሉ አቶ ገአስ መሳሪያ የታጠቀ ልዩ ሃይልን ዞን አምስት ላይ በማሰማራት ቅሬታውን እያሰማ ያለውን ወጣት የማስፈራርቱን ዘመቻ ቀጥሎበታል።

በአፋር ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ አመራር በክልሉ ባሉ ችግሮች ላይ መሰረታዊ የሚባሉ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ከነዋሪውና ከወጣቱ የቀረበለትን ጥያቄ ተግባራዊ አላደረገም በሚል ሰሞኑን ተቃውሞ ሲነሳበት ቆይቷል።

በተለይ የአፋር ክልል ወጣቶች በክልሉ ወረዳዎች የተካሄደው ማሻሻያ ጎሰኝነትን ላይ ያተኮረና የቡድን ስራ የሚሰራበት ነው በሚል ለክልሉ መስተዳደር ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ነው የአፋር የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር ለኢሳት የገለጹት።

ነገር ግን ዛሬ ላይ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡት ወጣቶች ማስፈራሪያና ከዛም አለፎ እንዲታሰሩ እየተደረጉ ነው ይላሉ።

ይሄን አይነቱ አሰራር ግን ሊቆም ይገባዋል ይላሉ አቶ ገአስ ።–ትላንት ያለፍንበትን አሰራር ለመመለስ አይደለም የታገልነው በማለት።

እንደ አቶ ገአስ አባባል ወጣቱ እስካሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ላይ ነው።

ነገር ግን አመራሩ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የማስፈራራቱን ስራ ቀጥሎበታል ባይ ናቸው።

አቶ ገአስ እንደሚሉት በክልሉ አሁን እየታየ ያለው ነገር ቀደም ሲል በህዝቡ ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዎች ተመልሰው ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ነው።

እነዚህ ሰዎች ደግሞ እንደ ሃገር የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚሰሩ ናቸው ብለዋል ከኢሳት ጋር በነበራቸው ቆይታ።

በክልሉ አሁን እየተደረገ ያለውን ሁኔታ ደግሞ የአፋር ህዝብ በዝምታ የሚያልፈው አይደለም ይላሉ።