ግንቦት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የሚታየው ከፍተኛ የዶላር እጥረት መባባሱን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።በአስመጭና ላኪነት ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ስራቸውን መስራት እንዳልቻሉ አቤቱታ
በማቅርብ ላይ ናቸው። በርካታ ፋብሪካዎችም በዶላር እጥረት የተነሳ የመለዋወጫ እቃዎችን ማስገባት አለመቻላቸውን እየገለጹ ነው። መንግስት የዶላር ችግር እንደሌለ በተደጋጋሚ ቢናገርም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህ እንደሚለይ
ነጋዴዎች ይገልጻሉ።
ለኢሳት የሚደርሱት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ የውጭ አገር ኢምባሲዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ዲፕሎማቶች በዶላር እጥረት የተነሳ ላለፉት 3 ወራት ደሞዝ አልተከፈላቸውም። ከዚህ ቀደም በኢሳት የቀረበውን ተመሳሳይ ዘገባ ተከትሎ
መንግስት በአፋጣኝ ለዲፕሎማቶች ክፍያ ቢፈጽምም፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በብዙ ኢማበሲዎች የሚሰሩ ሰራተኞች ደሞዝ ያልተከፈላቸው በመሆኑ ተቸግረዋል።
በዚህ አመት የታየው የዶላር እጥረት ከዚህ ቀደም ታይቶ ከነበረው እጥረት ጋር ሲነጻጻር የተራዘመ እና የከፋ መሆኑን ነጋዴዎች ይገልጻሉ።
የወጪ ንግድ መቀነስ፣ ዲያስፖራው በህጋዊ መንገድ የሚልከው ገንዘብ መጠን ማነስ፣ በወጪና ገቢ ንግድ መካከል ያለው ልዩነት መስፋት እንዲሁም በእቅድ ላይ ያልተመሰረቱ ወይም ለፖለቲካ ፍጆቷ እየተባሉ የሚሰሩ ኢኮኖሚ
አዋጭነታቸው ያልተረጋገጡ ፕሮጀክቶች መብዛት ወደ ውጭ በሙስና ስም ከሚወጣው ገንዘብ ጋር ተደማምሮ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈጠሩን ጥናቶች ያመለክታሉ።
የተወሰኑ ነጋዴዎች በገንዘብ በመደራደር ለሚፈልጉዋቸው ነጋዴዎች ብቻ ዶላር እየሸጡ ከፍተኛ ሃብት እየሰበሰቡ መሆኑም ነጋዴዎች ይናገራሉ።
መንግስት በቅርቡ ከአለማቀፍ የግል አበዳሪ ተቋማት 1 ቢሊዮን ዶላር መበደሩ ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው በላይ እጅግ የተጋነነ በጀት መመደቡ አነጋጋሪ ሆኗል። መንግስት ለ 2008 ዓም ወጪ 223 ቢሊየን 400 ሚሊዮን ብር አጽድቋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2007 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ያለውን የፌዴራል መንግስት 22 ነጥብ 6 በመቶ ለመደበኛ ፣ 37 ነጥብ 4 በመቶ ለካፒታል ወጪዎች ይውላል ተብሎአል።
ለክልሎች የሚሰጠው ድጋፍ 34 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን 5 ነጥብ 4 በመቶው ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያነት እንዲውል ተመድቧል።
በያዝነው 2006 በጀት ዓመት የጸደቀው 178 ቢሊየን 600 ሚሊዮን ብር ሲሆን ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 21 ቢሊየን ብር ያህል ጉድለት እንደነበረበትና ከበጀቱ 19 በመቶ ያህሉ በዕርዳታና በብድር የሚሸፈን ነበር።
የ2008 በጀት ከ2006 ጋር ሲነጻጸር በ44 ቢሊዮን 6 መቶ ሚሊዮን ብር መጨመሩን የገለጸው ዘጋቢያችን ይህን ያህል እጅግ የተጋነነና ኢኮኖሚው ሊያመነጨው ከሚችለው በላይ በጀት ለመያዝ የተገደደው የጀመራቸውና ዘንድሮ
የሚጠናቀቀውን የዕድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዱን ተከትሎ በበጀት እጥረት ያልተጠናቀቁ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመደጎም በማቀዱ ነው ብሎአል።
ይህን ከፍተኛ የበጀት ጉድለት የሚያስከትል የ2008 በጀት በፓርላማው ሲጸድቅ እየተረጋጋ ያለውን የዋጋ ንረት መልሶ እንዲያገረሽ ሊያደርገው ይችላል ሲል ባለሙያዎችን በማነጋገር ዘጋቢያችን ገልጿል።