የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቅርቡ ከአርባምንጭ 65 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዲካ ወረዳ ላይ አንድ ቤተክርስቲያን መቃጠሉን ኢሳት ዘግቦ ነበር። ሰሞኑን ችግሩ ተባብሶ የወረዳው ነዋሪዎች ቤተክርስቲያኑን ያቃጠሉት ሰዎች 3 የመንግስት ባለስልጣናት በመሆናቸው፣ ባለስልጣናቱ ለፍርድ ይቀረቡልን በሚል ተቃውሞ ማሰማት ጀምረዋል።
መንግስት ለጥያቄያቸው መልስ ለመስጠት ባለመቻሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአንድ ቀን ከቤታቸው ባለመውጣት ተቃውሞዋቸውን ገልጠዋል።
በሁኔታው የተደናገጡት ከፌደራል እና ከክልል የመጡ ባለስልጣናት ፣ ባለስልጣኖቹ ተይዘው ለፍርድ ቀርበዋል በሚል ቅስቀሳ ተቃውሞውን ለማብረድ ሞክረዋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናቱ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ማነጋገራቸውን ለማወቅ የታቸለ ሲሆን፣ የከተማው ነዋሪዎች እባካችሁ በሀይማኖትና በዘርለማጋጨት የምታደርጉትን እንቅስቃሴ አቁሙ ብለው ፊት ለፊት እንደ ነገሩዋቸው ታውቋል። ስብሰባው እየተካሄደ መሆኑንም ለማወቅ ተችሎአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጨንጫ ወረዳ ከወር በፊት አንድ የወህኒ ቤት ፖሊስ ታቦተ ህጉን ተሸክመው በሚሄዱት ካህናትና ምእመናን ላይ በከፈተው ተኩስ 1 ሰው ገድሎ 9 ማቁሰሉን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። የወረዳው ነዋሪዎች ዘገባው የደረሰውን ጉዳት በደንብ አላሳየም በሚል ቅሬታቸውን ገልጠዋል። ከነዋሪዎቹ ለመረዳት እንደተቻለው በእለቱ በደረሰ ጉዳት አንድ ሰው እጅና እግሩ መቆረጡን፣ ከሶስት ያላነሱት አሁንም በሞት አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ ሰላም በር በሚባለው አካባቢ ፣ ከማዳበሪያ ጋር በተያያዘ አንድ የግብርና የልማት ሰራተኛ ተገድሏል። ኢሳት በትናንት ዘገባው በጋሞ ጎፋ ዞን ዑባ ማሌ ዘባ ቀበሌ ሊቀመንበርና ጸሐፊው እዳ ሊያስከፍሉ ሲመጡ በአካባቢው ገበሬዎች ተደብድበው መገደላቸውን፣ በኡባ ማሌ ወረዳ ያላ ቀበሌ ውስጥ ደግሞ የወረዳው የሚሊሺያ አዛዥ በአካባቢው ነዋሪዎች በተመሳሳይ መንገድ መሞቱን መዘገቡ ይታወሳል።
በጋሞ ጎፋ ዞን በከሜላ ዛላ ዑባ ማሌ ወረዳ ደግሞ ሰሞኑን አንድ የመንግሥት ፖሊስ በመገደሉ መንግሥት በግልጽ ህዝቡን ማስጨነቅና ማስፈራራት ጀምሯል፡፡
በአሁኑ ጊዜም በጎፋ አካባቢ የገዜ ጎፋ ወረዳ ነዋሪዎች ማንኛውም የካቢኔ አባላት ወደ ቀበሌዎች ውስጥ እንዳይገቡ ወደ ጃውላና ባጋባርዛ የሚሄደውን መንገድ በእንጨት ግንድና አጠና በመዝጋት “ማዳበሪያ በፍላጎት እንጂ በግድ አይሰጠን፣ መሬታችን ለም ነው፣ ገንዘብ የለንም፣ እዳ አትቆልሉብን” በማለት የመንግስትን የሥራ እንቅስቃሴ ማስተጓጎላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ፍኖተ ነጻነት ዛሬ ባወጣው ዘገባ ደግሞ በደራሼ ወረዳ የተፈናቀሉ 892 አባወራዎች በከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ “በደራሼ ወረዳ ቀያማ ነዋሪዎች በመሬት ቅርምትና በዘረኝነት በተፈጠረ ግጭት 892 መኖሪያ ቤቶችና ግምታቸው ያልታወቁ ንብረቶች በእሳት በመውደማቸው ነዋሪዎቹ ወደ አጐራባች ቀበሌዎች ተሰደን እንገኛለን፡፡” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
“የአካባቢው ባለሥልጣናት ችግርን ከመፍታት ይልቅ በሕብረተሰቡ ላይ ችግር ሲፈጥሩና ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታ ሲያመቻቹ አለመታየታቸውን ፣ አስተዳደራዊ አቤቱታ ማቅረብም በወንጀል እንደሚያስከስስ ነዋሪዎች መናገራቸውን ፍኖተ ዘግቧል።
በተያያዘ ዜና ወደ ህትመት በመግባት ላይ እያለን በዚሁ ወረዳ ከየካቲት 2 እስከ የካቲት 4 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ሥልጠና ላይ የቆዩት የደራሼ ወረዳ አንድነት ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ አምሳሉ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ወረዳቸው በመጓዝ ላይ እንዳሉ ሆሳዕና ከተማ ላይ “የአካባቢው ፖሊሶች ባቀነባበሩት ሁከትና ትርምስ ተይዘው ታስረዋል።
“አቶ ተሾመ ሆሳዕና ከተማ እንደደረሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ሻንጣቸውን ነጥቀዋቸው በመፈተሻቸው ግራ ሲጋቡ ለፖሊሶች ሲያመለክቱ ፣ ፖሊሶቹ አንድነት ሽብር እንድትፈጽም አሰልጥኖ ለኮሃል በማለት ከፓርቲው ይዘውት የሄዱትን የፓርቲውን ስትራቴጂ ሰነድ፣ደንብና ፕሮግራም ነጠቀው ማሰራቸውን” ጋዜጣው ዘግቧል፡፡