ዓረና ትግራይ ፓርቲ ኢህአዴግን ክፉኛ ነቀፈ

የካቲት 6 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፓርቲዉ ማእከላዊ ኮሚቴ ከጥር 26 እስከ 28/ 2004 በመቀሌ ከተማ ባደረገዉ መደበኛ ስብሰባ በኢኮኖሚ፤ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አገሪቱና በተለይም የትግራይ ክልል የገጠሟቸዉን በገዢዉ ፓርቲ በመፈፀም ላይ ያሉ ህገወጥ ድርጊቶችን በዝርዝር ተመልክቷል።

ኢህአዴግ ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበና ሀብታም የገጠር ገበሬዎች በመፈጠር ላይ እንዳለ ቢናገርም እዉነታዉ ከዚህ የተለየ፤ የህዝቡ ኑሮ እጅግ የዘቀጠና ከቀን ወደ ቀን ድህንት እየተንሰራፋ፤ ረሃብ እየተስፋፋ፤ የኑሮ ዉድነት እየተባባሰ መሆኑን ገልጿል።

 ተራ የሸቀጦች የዋጋ ተመን እስከመስጠት የዘለቀ የመንግሰት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት፣ መንግስት ህገወጥ ገንዘብ አሳትሞ በገበያ ዉስጥ መርጨቱ፣ ገበያዉ ደረጃቸዉን ባልጠበቁ የቻይና ሸቀጦች መጥለቅለቁ፣ የኢኮኖሚ አመራር ድክመት በመኖሩና 40% ድረስ ያሻቀበዉ ከአለም በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘዉ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር አለመቻሉ የችግሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል።

ገዢዉ ፓርቲ የፖለቲካ ስልጣንና የኢኮኖሚዉን የበላይነት ለመቆጣጠር በሚከተላቸዉ ደካማ ፖሊሲዎች ምክንያት የአገሪቱን ሀብት በገፍ ከሚዘርፉት የመንግሰት ባለስልጣኖችና ተባባሪዎቻቸዉ በስተቀር የተራዉ ህብረተሰብ ኑሮ በከፋ ደረጃ ላይ መዉደቁን ፓርቲዉ በጥልቀት ተመልክቶታል። 

የመንግስት ብልሹ አስተዳደር የፈጠረዉ ሙስና እንዳለ ሆኖ በቅርቡ ሕዝብና የህዝብ ወገኖች ሳይመክሩበት በችኮላ የወጣዉ የከተማ ቦታን ወደ ሊዝ የሚያስገባዉ አዋጅ የዜጎችን ንብረትና ሃብት የማፍራት መብት የሚፃረር ኢፍትሃዊና ኢዲሞክራሲያዊ እንደሆነ አመልከቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መንግሰት በትግራይና በሌሎችም አካባቢዎች ድሃዉን የህብረተሰብ ክፍል በሃይል ከይዞታዉ በማፈናቀል፡ መኖሪያዉን ያለ ምትክና ካሳ እያፈረሰ መሬቱን ለገዢዉ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣኖችና አባላት እንዲሁም “ልማታዊ ባለሃብቶች” ከሚላቸዉ ጋር ከከተሞች ማስተር ፕላን ዉጭ በርካሽ ዋጋ ቅርምት ላይ ማዋሉ መሆኑን አብራርቷል።

ዜጎች በማህበር ተደራጅተዉ የቤት መስሪያ ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ አለመኖሩን የጠቀሰዉ ዓረና የትግራይ ተወላጆች መብታቸዉን ለማስጠበቅ በሚወስዱት እርምጃ በመንግስት የፀጥታና የደህንነት ሃይሎች ህገወጥ ወከባና እንግልት እንደሚደርስባቸዉ አመልክቷል።

ሙስናና ብልሹ አስተዳደር በትግራይ ክልል ዉስጥ ከፉኛ መንሰራፋቱ ያሳሳበዉ መሆኑን የገለፀዉ ዓረና ፤ በመንግሰት የግዢ አፈፃፀም፤ በመሬት አሰጣጥና በፍትህ አካላት ተግባር ዉስጥ እንዲሁም በግብር ክፍያ፤ በንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ግልፅነት የጎደላቸዉ የጨረታ አፈፃፀሞች እየተበራከቱ ነው ብሎአል።

የማእከላዊ ኮሚቴዉ የገዢዉ ፓርቲ ከፍላጎትና ከፈቃደኛነት ዉጭ በተለያየ ጥቅምና መንገድ አባላትን ለመግዛት፤ለመደለልና ለመመልመል የሚፈፅመዉ ደካማ ተግባር ፣ በየስራ መደቡ እዉቀትና ልምድ የሌላቸዉ ሰዎች በሃላፊነት እንዲቀመጡ በማድረግ፤ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር እንዲሰፍን ከማድረጉም በላይ የብቁ  ባለሙያዎችን ፍልሰት በማስከተል ላይ መሆኑን አስገንዝቧል።

 በትግራይ ክልል ስር እየሰደደ በመሄድ ላይ ያለዉ ሙስናና ብልሹ አስተዳደደር የትምህርቱ ዘርፍ የጥራት ደረጃ እንዲወድቅና በክልሉ ያለዉ የስራ አጥነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ አንዲደርስ ማድረጉን አመልክቷል።

የገዢዉ ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ የክልሉን  ህዝብ በነፃነት የመደራጀት፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በማፈን፤ህዝቡ የግል የነፃ ህትመት ዉጤቶችን እንዳያገኝ በማገድና ህዝባዊ ወገናዊነት ያላቸዉን ፀሃፊዎች በማዋከብና በማንገላታት፤ አልፎ ተርፎ በደህንነት፤ በፖሊስና በሚሊሺያ አካላቱ አማካይነት እንዲሁም የኮሙኒቱ ፖሊስ፤ የሴቶች ሊግ፤ የገበሬ ማህበር፤ የገዢ ፓርቲ ኮሚቴዎች፤የልማት ኮሚቴ፤ ወዘተ የሚሉ ከቤተሰብ እስከ ፓርቲ የበላይ አካል በሚደርስ ስር የሰደደ የቁጥጥር ስርኣት በመዘርጋት  የዜጎችን ፖለቲካዊና ሰብኣዊ መብቶች በመርገጥና በማፈን ላይ እንዳለ አስታዉቋል።

ዓረና ትግራይ ከዚህ በተጨማሪ በገዢዉ ፓርቲ ከፍተኛ የማእከላዊ ኮሚቴ አመራሮችና፤ ዳኞችና አቃቢያነ ህጎች አማካይነት ስልጠና በመስጠት ስም የአስተዳደርና የፍትህ ስርኣቱን ሙሉ በሙሉ የህወሃት/ኢህአዴግ የመጠቀሚያ መሳሪያ በማድረግ ላይ እንዳለ አውስቷል። 

በመጨረሻም ህወሃት/ኢህአዴግ፤ የመንግሰት ስራና የፓርቲ ስራ ለይቶ የመንግስት የስራ ጊዜ መንግስት ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸዉ ሆነዉ እንዲሰራባቸዉ፤ በግብር ከፋዩ ገንዘብ ደመወዝ የሚከፈላቸዉ የገዢ ፓርቲ አባል ካድሬዎች መላዉ የስራ ጊዜ ህዝብን በማገልገል እንዲያዉሉ፤  መንግስት አዋጆች፤ ደንቦችና መመሪያዎች ከማዉጣቱ በፊት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፤ ጉዳዩ የሚያገባቸዉን ባለሙያዎች፤ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሲቪል ማህበራት ለህዝብ ግልፅ በሆነ እንዲመክሩበት እንዲያደርግ ጠይቋል።

እንዲሁም  የአንድ አገር  ህዝብ ዋናዉ እሴት የህዝቡ አንድነትና በጋራ እሴቶቹ መግባባት፤ መከበር መሆኑ ግልፅ ሲሆን ህወሃት/ኢህአዴግ ግን ከታሪክ ማበላሸት ዘመቻ ጀምሮ ህዝብን በመከፋፈል ፣ በከፋፍለህ ግዛ ሴራ መጠመዱን እንዲያቆም ጠይቋል።