”የዘንድሮው ምርጫ፤ ምርጫም፣ቅርጫም አይደለም”ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናገሩ

የካቲት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- መራጮች ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት ለዘንድሮው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ  ዜጐች ቤታቸው በራፍ እየተንኳኳ አስጨናቂ በሆኑ የማግባባት ሂደቶች፤ ሕጉ እና መመሪያው የሚጠይቀው አንዱም መስፈርት መሟላቱ ሳይረጋገጥ ‹‹ሰው›› መሆኑ ብቻ እየታየ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ሲገደዱ ነበር።

በምርጫ 97 ወቅት በመራጭነት ለመመዝገብ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው የነበሩት መስፈርቶች በዘንድሮው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ በቸልተኝነት መታለፋቸውን የጠቆሙ መራጮችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ የነዋሪነት ማረጋገጫ የቀበሌ መታወቂያ፣ በቀበሌው የነበረው የነዋሪነት ዘመን ቆይታና ከ18 ዓመት በላይ የሚለው የዕድሜ ገደብ በሚገባ መሟላቱ ሳይረጋገጥ የመራጭነት መታወቂያ ካርድ መሠጠቱን ገልጸዋል፡፡

ተስተውለዋል በተባሉት ችግሮች ዙሪያ አድማስ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ ይስማው ጅሩ ፤ አንድ ዜጋ ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ ብቻ የመራጭነት ካርድ እንደሚሰጠው በመጥቀስ ‹‹በዚህኛው የመራጮች ምዝገባ ሂደትም ይኸው ተግባራዊ ተደርጓል፡፡‹‹እነዚህ ሁሉ መመዘኛዎች ሳይሟሉ መራጮች እየተመዘገቡ ነው የሚል አቤቱታ እስከዛሬ ከየትኛውም ወገን አልደረሰንም”በማለት አስተባብለዋል።

የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ይህን ቢሉም  መራጮች ግን ያለምንም መስፈርት  በጫና መመዝገባቸውን ነው የሚናገሩት።

ምርጫ 97ን ከአሁኑ ምርጫ ጋር በማነጻጸር አስተያየታቸውን የሰጡ ተመዝጋቢዎች፤ያን ጊዜ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በተጠቀሱት መስፈርቶች መሠረት፣ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጎ የሚሰጥ ሲሆን መስፈርቱን ያላሟላ መራጭ ካርዱን እንዳይወስድ ይከለከል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለዘንድሮው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ግን ዜጐች ቤታቸው በራፍ እየተንኳኳ ሕጉ እና መመሪያው የሚጠይቀው አንዱም መስፈርት መሟላቱ ሳይረጋገጥ አስጨናቂ በሆኑ የማግባባት ሂደቶች፤   የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ሲገደዱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በመጪው ሚያዚያ  የሚካሄደውን ምርጫ ዝግጅት ከ97 ምርጫ ጋር ያነፃፀሩት የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፤‹‹አንድ ዜጋ ምርጫ የመምረጥ ወይም ያለመምረጥ፤ የምርጫ ካርድ የመውሰድ ወይም ያለመውሰድ መብቱ የተጠበቀ መሆን ሲገባው የግዴታ ግፊት በማድረግ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ እንዲመረጥ መቀስቀስ፤ የዴሞክራሲ ሂደት መክሸፉን ያመላክታል›› ብለዋል፡፡

ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤‹‹ዜጐች ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ መቀስቀስ ተገቢነት ያለው ቢሆንም ፤የዚህኛው ምርጫ አካሄድ ግን ይለያል፤ያን ጊዜ ምርጫ ካርድ ለመውሰድ አንድም መስፈርት ማጓደል ክልክል ነበር፤ አሁን ግን የተመዝጋቢውን ቁጥር በማግዘፍ ምርጫ ያለ ለማስመሰል የምርጫ ካርድ ዕደላ ተያይዘዋል፡፡›› ብለዋል፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ የሚደረገውን ሁሉ ጠንቅቆ ያውቃል›› ያሉት ፕ/ር መረራ፤ “ከዚህ በኋላ ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም እንጂ የዴሞክራሲ ግንባታ የሚባለው ነገር አቁሟል” ብለዋል፡፡

‹‹የዚህ የመራጭነት ምዝገባ ቅስቀሳ ስልት ውጤትም አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዐትን መገንባት ነው›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ‹‹የ1997 ዓ.ም ምርጫ -ቢያንስ ምርጫ የሚመስል ነገር ነበረው፤ የአሁኑ ግን ምርጫም ፣ቅርጫም መሆን አይችልም፡፡›› ሲሉ ተችተዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሣ፤በበኩላቸው፤ “ገዥው ፓርቲ እርሱን የሚመርጠውንና የማይመርጠውን ለይቶ ስለሚያውቅ፣ የሚመርጠውን ብቻ ለይቶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ ይገፋፋል የማይመርጠው መስሎ ከታየው ብዙ መመዘኛዎችን እያስቀመጠ ከተሣታፊነት እንዲገለል ያደርጋል፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው” ብለዋል፡፡

በዚህኛው የመራጮች የምዝገባ ሂደት ሁለት ጉዳዮችን መታዘባቸውን የጠቀሱት የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ  አንደኛው ‹‹ኮሙኒቲ ፖሊስ›› የሚባሉ የመንደር ውስጥ ፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ሥራቸው ጥበቃ ሆኖ ሳለ በየቤቱ እየዞሩ “ተመዝገቡ” ማለታቸው ሲሆን ፤ ሌላኛው ደግሞ  ሦስት እና አራት ጊዜ በየቤቱ በመመላለስ “ሂዱና ተመዝገቡ” እያሉ የሚቀሰቅሱ አካሎች መኖራቸውን ነው፡፡

ይህ ፤ በተዘዋዋሪ ኢህአዴግን ምረጡ ማለት እንደሆነና በዜጐች የግል ውሣኔ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት ሊቆጠር እንደሚችል ዶ/ር ነጋሶ አስረድተዋል፡፡