ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለስራ የተቀመጡ 18 አምባሳደሮችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጠራ

የካቲት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሚኒስቴሩ ይህን እርምጃ የወሰደው ባለፈው ሀሙስ የፓርላማ አባላት ለአዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሐኖም ጥያቄ ካቀረበ በሁዋላ ነው። የፓርላማ አባላት “በአንድ አገር ውስጥ ሁለት አምባሳደሮችና ሁለት ምክትሎች ይመደባሉ፣ ስራቸው ምንድነው?” በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሚኒስትሩም ” ምን እንደሚሰሩ አላውቅም” የሚል መልስ መስጠታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።

በአጠቃላይ 30 አምባሳደሮችና ምክትሎች ያለምንም ስራ ደሞዝ እየተከፈላቸው እንደሚገኙ የዘገበው ጋዜጣው፣ ከእነዚህ መካከል 18ቱ በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተጠርተዋል ብሏል።

ወደ አገራቸው ከተመለሱ 18 አምባሳደሮች መካከል 2ቱ ብቻ ስራ ሲገኝላቸው፣ 16ቱ ደሞዝ እየተከፈላቸው ያለምንም ስራ መቀመጣቸው ታውቋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ መንግስት በእየአገሩ ሁለት ሁለት አምባሳደሮችን ሲሾም ትልቅ ስህተት ሰርቶ ነበር ያሉ ሲሆን፣ የተንሳፈፉ አምባሳደሮች ቦታ ከተገኘላቸው ሊመደቡ እንደሚችሉ ቦታ ካልተገኘ ግን ምንም ሊያደርጉዋቸው እንደማይችሉ ገልጸዋል።

አብዛኞቹ አምባሳደሮች የተሾሙት በፖለቲካ ታማኝነታቸው ሲሆን፣ የመለስ መንግስት አባሎቹን ላለማስከፋት ሲል በአንድ ኢምባሲ ውስጥ ሁለት ሁለት አምባሳደሮችን መሾሙ ይታወቃል።

አምባሳደሮች ላለፉት ሁለት አመታት ያለምንም ስራ ከፍተኛ ገንዘብ ሲከፈላቸው ቆይቷል።