በትላንት አርብ የጁማ ጸሎት ተሳትፈዋል የተባሉ ሙስሊሞች ታሰሩ

የካቲት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ ከአዲስ አበባ የላከው ሪፖርት እንዳመለከተው ከፍተኛ ቁጥር ባስተናገደው የትናንት የጁማ ተቃውሞ በአስተባባሪነት የተጠረጠሩ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እየተለቀሙ በመታሰር ላይ ናቸው።

በመርካቶ፣ ፒያሳ ፣ ጉለሌ፣ ሰባተኛ እና በሌሎችም አካባቢዎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሙስሊሞች ተይዘው ታስረዋል።

ከታሰሩት መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ፣ አንዳንዶች ወደ ማእከላዊ እስር ቤት ሌሎች ደግሞ በየአካባቢያቸው ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች ተወስደዋል።

በየሰፈሩ የሚገኙ የኢህአዴግ አባላት ከጸጥታ ሀይሎች ጋር አብረው በመዞር ጥቆማ ሲያካሂዱ  መዋላቸውን ሪፖርተራችን የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የመጅሊስ አመራሮችን በአደማ አባ ገዳ አዳራሽ ሰብስቦ እያወያያቸው መሆኑ ታውቋል።

በተመሳሳይ ዜናም  በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች ጥያቄያቸውን ለዩኒቨርስቲው ዲን አቅርበዋል። ተማሪዎቹ ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል “የጠፉት ሙስሊም ወንድሞቻችን ያሉበት ቦታ ይነገረን፣ ወንጀለኛ የተባሉት በምን ምክንያት ነው?” የሚሉት ይገኙበታል። የዩኒቨርስቲው ሀላፊም   አንደኛው ተማሪ  በአሸባሪነት ተጠርጥሮ ወደ አዲስ አበባ መወሰዱን ፣ ሌሎች ሁለት የጠፉ ተማሪዎችን በተመለከተ ግን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ከሙስሊም ኢትዮጵያውያን ዜና ሳንወጣ የአንደኛው ተከሳሽ የአቶ አቡበክር አህመድ ባለቤት የሆኑት  ወ/ሮ ሩማና ሡልጣን ጀሀዳዊ ሀረካት በሚል ርዕስ በኢቲቪ የተላለፈውን ፊልም አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ  ‹‹በፊትም የባለቤቴን ንጹሕነት ስለማውቅ አከብረው ነበር፤ አሁን ይብሱኑ እንዳከብረው አደረገኝ፤›› ብለዋል።

በዶክመንታሪ ፊልሙ አቶ አቡበከር ‹‹ዋናው ዓላማ እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ነው፤›› የሚል ንግግር ሲናገር መስማቷን የጠቀሰችው ወ/ሮ ሩማና፣ ‹‹ባለቤቴ ይህን ያለው የግብጹ ሙስሊም ብራዘርሁድ ዓላማ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ቀርቦለት የሰጠው ምላሽ›› እንደኾነ ታስረዳለች፡፡ ይኹንና በፊልሙ ቅንብር የእርሱ ንግግር ተቆርጦ ስለዓላማው እንደተጠየቀ በማስመሰል መቅረቡን በማስረዳት ወ/ሮ ሩማና ትከራከራለች፡፡

ጅሀዳዊ ሀረካት የሚለው ፊልም የተሰራው ቤተሰቡ እንዲሸማቀቅና አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግና ተከሳሹን ሕዝብ እንዲጠላው በማቀድ ነው ያሉት የተከሳሽ አቡበከር ባለቤት፣ ‹‹እውነታው ግን ወደፊት የሚወጣ ነው፤ አሁንም ቢሆን በእውን እርሱ የተናገረው ሳይሆን የተቀነባበረ ሥራ መኾኑን ሕዝቡ ይረዳል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡