የጸጥታ ሹሙ የኦሮሚያን መሬት ለሶማሊ ክልል አሳልፈን አንሰጥም አሉ

የካቲት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ላለፉት 4 ቀናት በተካሄደው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከፍተኛ   አጀንዳ ሆኖ የቀረበው በክልሉና በሶማሊ ክልል መካከል ያለው የብሄር ግጭት ነው። ከህመማቸው በመጠኑም ቢሆን አገግመው በስብሰባውላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ አቶ አለማየሁ አቶምሳ እና የክልሉ የጸጥታ ሹም ፍቃዱ ሰቦቃ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ መልስ ለመስጠተ ሞክረዋል።

ከምስራቅ ኦሮሚያ እና ከቦረና ዞን የመጡ የምክር ቤት አባላት የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበሮች በተደጋጋሚ በመግባት በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን ገድለው፣ በብዙሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ማፈናቀላቸውን ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማቅረብ ለባለስልጣናቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ኩምቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያዎች እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል  በተካሄደው ግጭት በርካታ ኦሮሞዎች መገደላቸውን፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩትም መፈናቀላቸውን የምክር ቤት አባላቱ ገልጠዋል።

እንዲሁም በሞያሌ አካባቢ በቦረና ኦሮሞ እና በጋሪ ሶማሊዎች መካከል በደረሰው ግጭት ከ40 አላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ከ20 ሺ በላይ የሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን ግለጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ የክልሉ መንግስት ዝምታን በመምረጡ የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እንዲያደርሱ እድል ሰጥቷቸዋል በማለት ወቀሳ አቅርበዋል።

የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት  ፈቃዱ ሰቦቃ ምንም እንኳ በሁለቱ ብሄሮች መካከል ያለው ግጭት መንስኤ የግጦሽ መሬት እጥረት ቢሆንም፣ ድንበሩ እስከ ዛሬ ድረስ አለመካለሉ ችግሩን አባብሶታል ብለዋል። እንደ ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊው አነጋገር በድንበር ላይ ያሉ ህዝቦች ማንነታቸውን ለመወሰን ባለመቻላቸው የድንበር ማካለሉ ሊካሄድ አልቻልም። ድንበሮቹ በትክክል ቢካለሉ ኖሮ ችግሩን ለመቆጣጠርና  ለመቅረፍ ይቻል እንደነበር የገለጡት ባለስልጣኑ፣ መፍትሄውም በቶሎ ድንበሮችን ማካለል ነው ብለዋል።

ድንበሮቹ ሲካለሉ በአካባቢው የሚኖሩ አርብቶአደሮች ከክልል ወደ ክልል ለመዘዋወር የይለፍ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት ሊጠየቁ የሚችሉበት እድል ሰፊ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።

ዛሬ ጧት በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ በትምህርት ጥራት፣ በግብርና፣ በኑሮ ውድነት እና በህዝቡ ተነሳሽነት እጦት ዙሪያ ውይይቶች ተካሂደዋል።

የግብርናው ምርት አድጓል እየተባለ ቢነገረም ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ እየተጎሳቆለ መሆኑንና ህዝቡን ቀርበው ለማነጋገር እንደቸገራቸው የምክር አባላት ገልጸዋል። የምክር ቤት አባላቱ የመረጣቸውን ህዝብ ሄደው በሚያገኙበት ወቅት ከህዝቡ የሚነሱ በርካታ ችግሮችን መልሰው ለምክር ቤቱ ቢያቀርቡም በስራ አስፈጻሚው በኩል መልስ ሊሰጥ ባለመቻሉ ህዝቡን ማነጋገሩ ትርጉም የሌለው ሆኗል በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡ የምክር ቤት አባላት ነበሩ።

አቶ አለማየሁ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ የሚታየው ሙስናና ምዝበራ ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱን አምነዋል። የመንግስት ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመዘበረ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩን ለማቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱንም አልሸሸጉም።