የዓዲግራት ዩንቨርሲቲ የህክምና ተማሪዎች ተገቢውን ትምህርት ማግኘት ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን አቋረጡ።

የዓዲግራት ዩንቨርሲቲ የህክምና ተማሪዎች ተገቢውን ትምህርት ማግኘት ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን አቋረጡ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 05 ቀን 2011 ዓ/ም ) በዓዲግራት ዩንቨርሲቲ የህክምና ተማሪዎች በተቋሙ አስተዳደር ለሚደርስባቸው አስተዳደራዊ በደሎች መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት አልቻሉም። ይህን ተከትሎ ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ መከታተል ባለመቻላቸው ለማቋረጥ መገደዳቸውንና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠን ሲሉ ለጤና ጥበቃ ሚንስቴር በደብዳቤ አሳውቀዋል።
የመማር ማስተማሩ አስመልክቶ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዳሉት የ6ኛ ዓመት ተማሪዎች ባለፉት 9 ወራት ብቻ ለ5 ወራት ከመማር ማስተማር ውጪ ነበሩ። የ5ኛ እና የ4ኛ ዓመት ተማሪዎች /በበኩላቸው በተመሳሳይ ተገቢውን የመማር እድል በማጣታቸው ከተመሳሳይ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ወደኋላ ቀርተዋል።
ዩንቨርሲቲው በበኩሉ የአስተማሪ ስፔሻል ሃኪሞች እጥረት፣ ያሉትም ጥቂት ስፔሻሊስት ሃኪሞች የሥራ መደራረብና የደመወዝና የጥቅማጥቅም መብት አለመከበር፣ ከሌሎች ዩንቨርሲቲዎች የሚያመጣቸው የተጋባዥ መምህራን ጋር በተመሳሳይ የደመወዝና በጥቅማጥቅም ጉዳይ አለመስማማት ያስከተለው የተጋባዥ መምህራን እጥረት፣ ዩንቨርሲቲው የራሱ የሆነ የማስተማሪያ ሆስፒታል የሌለው ሲሆን የዓዲግራት ጠቅላላ ሆስፒታልም ከተማሪዎቹ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ፣ በሆስፒታሉ በቁጥርም ይሁን በዓይነት በቂ የሆነ ታካሚዎች አለመገኘትን፣ በሆስፒታሉ በቂ የሆነ የህክምና መገልገያ እና የማስተማሪያ ቁሳቁስ አለመኖር፣ የተመደበለትን በጀት በራሱ ማንቀሳቀስ አለመቻሉን በምክንያትነት አቅርቧል።
የዩንቨርሲቲው አስተዳደር ተማሪዎቹ የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች ያለመቀበል፤ ወይም ከተቀበሉ በኋላ መፍትሔ ያለመስጠት፣ ለህክምና ትምህርት የሚሰጡት በጀት ማሳነስና ለችግሮቹ ትኩረት ያለመስጠትና በመጠናቸው ልክ አለመረዳትና በቸልተኝነት በማለፍ ችግሮቹ እንዲባባሱ አድርገዋል።
የሕክምና ትምህርት ከፍተኛትኩረት የሚሻ የትምህርት መስክ በመሆኑ መንግስት ትኩረት በመስጠት ለጥያቄያቸው መፍትሔ እንዲሰጠን ሲሉ ለጤና ጥበቃ ሚንስቴር እና በግልባጭ ለዓዲግራት ዩንቨርስቲ ቦርድ፣ ለዓዲግራት ዩንቨርስቲ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት፣ ለዓዲግራት ዩንቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እናለ ዓዲግራት ዩንቨርስቲ ሕክምና ትምህርት ቤት በደብዳቤ አሳውቀዋል።