የቀደሞው የመረጃና ደህንነት ሰራተኛ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠባቸው።

የቀደሞው የመረጃና ደህንነት ሰራተኛ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠባቸው።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 05 ቀን 2011 ዓ/ም ) ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ በተዘጋጀው የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ ወቅት የተፈጸመውን የሽብር ድርጊት አቀነባብረዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ተጨማሪ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።
ባለፈው ቀጠሮ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ቤት ውስጥ የተገኘውን ቦምብ እና በመስቀል ዓደባባይ ከፈነዳው ቦምብ ቅሪት አካል በማመሳከር አጠናቆ ለማቅረብ የአስር ቀናት ቀጠሮ መውሰዱ ይታወሳል። ነገርግን መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ቀናት ውስጥ የቴክኒክ ምርመራውን ማጠናቀቅ አለመቻሉን ለችሎቱ በመግለጽ ተጨማሪ የአስር ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ለችሎቱ አመልክቷል።
ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ፖሊስ ተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶታል። የዛሬውም የመጨረሻ ቀጠሮ ተብሎ ነበር። መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ አይገባውም። በተጨማሪም አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የፍርድ ቤቱን ሂደት በአካል ቀርበው ሳይከታተሉ የስም ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙብኝ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድልኝ ሲሉ ለችሎቱ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የከሰሳሽ መርማሪ ፖሊስን እና የተከሳሽን ቃል ካዳመጠ በኋላ የተዛባ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ በህግ እንደሚያስጠይቅ በመግለጽ፤ ይህን በሚፈጽሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብሏል። ለመርማሪ ፖሊስ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ፖሊስ የጠየቀውን የአስር ቀናት ቀነ ቀጠሮ ውድቅ በማድረግ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።