መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጨፌ ኦሮምያ ትናንት የጀመረውን የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ ሲያጠናቀቅ ምክትል ጠ/ሚኒስትር እና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰትር የሆኑትን አቶ ሙክታር ከድርን በፕሬዚዳንትነት፣ እንዲሁም አቶ ለማ መገርሳን በአፈ ጉባኤነት መርጧል።
ምንም አይነት ተወዳዳሪ እጩ ባልቀረበበት የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጽ ሳይሰማ ፕሬዚዳንቱም አፈ ጉባኤውም ተመርጠዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት አፈ ጉባኤው የፕሬዚዳንቱን ስም ጠርተው እንዲያጸድቁ እስከሚጠይቁዋቸው ድረስ የእጩዎችን ስም እንኳ እንደማያዉቁ ሂደቱን የተከታተለው ዘጋቢያችን ገልጿል።
ካፒታል የተባለው በአገር ውስጥ የሚታተመው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የኦፒዲዮ ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ይሾማሉ ሲል በሰበር ዜና ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል።
ኢሳት በትናንት ዘገባው ወ/ሮ አስቴር ማሞ የክልሉ ምክር ቤት አባል አለመሆናቸውን በመግለጽ ዘግቦ ነበር። ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ሰዎች ለመረዳት እንደተቻለው ወ/ሮ አስቴር ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር አለባቸው።