በኦሮምያ ክልል በጉጂ ዞን የተፈጠረው ግጭት

መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መጋቢት 16፣ 2006 ዓም ከጉጂ ዞን ዋና ከተማ ስያሜ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ግጭት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች እንደሞቱ የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ግጭቱ የጉጅ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ነገሌ ቦረና ፣ ነገሌ ብቻ ተብላ እንድትጠራ የመንግስት ባለስልጣናት ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎ የቦረና ተወላጆች ተቃውሞ በማስነሳታቸው መነሳቱ ታውቋል። የቦረና ተወላጆች ታሪካዊቷ የነገሌ ቦረና ከተማ ስያሜዋን እንደያዘች በጉጂ ዞን ትተዳደር የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ የጉጂ ዞን ባለስልጣናት በበኩላቸው ነገሌ ቦረና ነገሌ ብቻ ተብላ እንድትጠራ ውሳኔ አሳልፈዋል።
በዚሁ ሰበብ በተፈጠረ ግጭት በሊበን ወረዳ መጋዮ እና ቃርሳ-ማሌ ቀበሌዎች፣ ዲዳ ሳለ እና ላጋ ጉላ መንደሮች ቁጥራቸው ከ12 ያማያንሱ ሰዎች ሲገደሉ፣ 28 የሚጠጉ ደግሞ ቆስለዋል። አንዳንድ ወገኖች የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ይሆናል ይላሉ። ግጭቱ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ወደ ሌሎች ቀበሌዎች እየተዛመተ መምጣቱንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። እስካሁን የፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው አለመሰማራቱም ታውቋል።
በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን አካባቢው የሲዳሞ ክፍለሃገር ተብሎ ይጠራ እንደነበር፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ ሲዳማና ቦረና በሚል ለሁለት መከፈሉን እንዲሁም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ቦረና ለሁለት ተከፍሎ ቦረና ዞንና ጉጂ ዞን መባሉን የዞኑ የአንድነት ተወካይ እና የአካባቢው ሽማግሌ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ ለኢሳት አስረድተዋል።
ጉጂ ዞን ክብረመንግስት፣ ቦረና፣ ሻኪሶ፣ ሀርቀሎ፣ ዋደራና ሊበን ወረዳን በማካተት ነገሌ ቦረናን ዋና ከተማው አድርጎ ሲከለል፣ ቦረና ዞን ደግሞ ሞያሌን፣ ያቤሎ፣ አገረማርያም፣ ተንተሌ፣ አሬሮ፣ ገለባና አባያን፣ ዋና ከተማውን ያቤሎ አድርጎ ተዋቅሯል።
በሁለቱም ዞኖች ቦረናዎችና ጉጂዎች ለረጅም ጊዜ ተስማምተው ይኖሩ እንደነበር የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ግጭቱ ሆን ተብሎ በሁለቱ ነዋሪዎች መካከል ልዩነት ለመፍጠር ተብሎ የተቀሰቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር አደረግነው ሙከራ በስልክ መስመር ችግር ምክንያት ሊሳካልን አልቻለም።