ወንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙሉ የፀጉር አቆራረጥ ስታይላቸውን እንደ ሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዲያደርጉ ሰሜን ኮሪያ መመሪያ አወጣች።

መጋቢት ፲፰ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ራዲዮ ፍሪ ኤሺያን በመጥቀስ ቢቢሲ እንደዘገበው፣መመሪያው መጀመሪያ የተላለፈው በዋና ከተማዋ በፒዮንግያንግ  ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።

በአሁኑ ወቅት በ ሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙሉ አዋጁ ተግባራዊ እየሆነ መምጣቱን የዜና አውታሩ ጠቁሟል።

በወጣት ፋሽን ተከታዮች  “ስታይል” ጸጉራቸውን ከተቆረጡ የሰነበቱት  ወጣቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን፤ ይባስ ብሎ ወንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም  እንደ እርሳቸው እንዲቆረጡ አዋጅ ማውጣታቸው፤  በተለይ በምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሀን ዘንድ ስላቅን ፈጥሯል።አዋጁን በርካታ  የሰሜን ኮሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ቢቀበሉትም፤ የተወሰኑት ቅሬታ እንዳላቸው ተመልክቷል።

የሀገሪቱ ሚዲያዎች፦“የሶሻሊስታዊ ስርዓት አኗኗራችንን ለማጠናከር፤ ጸጉራችንንም በተመሣሳይ ስታይልና ቅርጽ እንቆረጥ” የሚል ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ቀደም ሲል ሀገሪቱን ለ 17 ዓመታት ያስተዳደሩት እና  የአሁኑ  መሪ አባት የነበሩት ሟቹ የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኢል፤ ኮሪያዎች ረጂም መስለው እንዲታዩ  በሚል  ልክ አሁን ልጃቸው እንደደነገጉት ዐይነት“ ከጎን እና ከጎን ተላጭተው መሀል ላይ ተለቅ ያለ ቁንጮ የሚታይበትን እና “ቡፋንት” ተብሎ የሚጠራውን የፀጉር ስታየል እንዲቆረጡ አውጀው ነበር።