የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ታሪካዊ የተባለ ውሳኔ አሳለፈ

ግንቦት ፬ (አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዜጎችን ከመንግስታዊ ስለላ ለመታደግ የተቋቋመው ድርጅት የእንግሊዝ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን ከሶ አስደሳች የፍርድ ውሳኔ ማግኘቱን ገልጿል።

ጋማ ኩባንያን ፊን ፊሸር እየተባለ የሚጠራውን የኮምፒዩተርና የስልክ የመረጃ መጥለፊያ ሶፍት ዌር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሰብአዊ መብቶችን ለሚጥሱ አገሮች መሸጡ በካናዳው ሲትዝን ላብ ላብራቶሪ መረጋጋጡን ተከትሎ ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በአገር ውስጥ ገቢና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ላይ ክስ መመስረቱ ይታወቃል።

እንግሊዝ የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤት ከአገሪቱ የሚወጡ ምርቶች በቂ ቁጥጥር ሳይደረግባቸው እንዲወጣ ፈቃድ ሰጥቷል በሚል ነው ክስ የተመሰረተበት።

ፍርድ ቤቱ የአገር ውስጥና የጉምሩክ መስሪያ ቤት አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል። ኮምፒተራቸው የተሰለለባቸው ዶ/ር ታደሰ ብሩ ውሳኔው  አስደሳች  ነው ብለዋል።