የእሳት አደጋ መኪና አጠቃቀም የፈጠረው ውዝግብ ለከፍተኛ ንብረት መውድም መንስኤ እየሆነ ነው

ግንቦት ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ አስኮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ቤት የሆነው ቲሻየር ሆም በተቃጠለበት ወቅት ነዋሪዎች ለአዲስ አበባ እሳት አደጋ መከላከያ መስሪያ ቤት የድረሱልን ጥሪ ቢያቀርቡም ፣ መስሪያ ቤቱ ግን የኦሮምያ ክልል ሳይፈቅድ መግባት አልችልም በሚል ምክንያት በተፈጠረው መዘግየት በቤቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ከመስሪያ ቤቱ ሰዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከዚህ ቀደም ብሎ ሱሉልታ አካባቢ ተከስቶ በነበረው ቃጠሎ ፣ የእሳት አደጋ መስሪያ ቤቱ ወደ ክልሉ እንዲገባ ፈቃድ በመጠየቅ ሂደት ላይ እያለ እሳቱ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱና በዚህም ሳቢያ የእሳት ማጥፊያ መኪኖቹ ዘግይተው በመድረሳቸው የተበሳጨው ነዋሪ ፣ በእሳት አደጋ መከላከያ መኪና ላይ በመወደው እርምጃ ግምቱ ከ180 ሺ ብር በላይ የሆነ ንብረት እንዲወድም አድርጓል።

የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ መኪና ወደ ኦሮምያ ክልል ገብቶ ስራ ለመስራት ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልገው በመሆኑና ፈቃዱንም ለማግኘት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣  በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች የእሳት አደጋ በሚያጋጥማቸው ጊዜ አፋጣኝ መልስ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ምንጮች ገልጸዋል።

ሰሞኑን በሱሉልታ ለወደመው የእሳት አደጋ መኪና የቡራዩ ማዘጋጃ ቤት አስፈላጊውን ካሳ እንደሚከፍል አስታውቋል።

የእሳት አደጋ መከላከያ ድርጀቱ  በሚሰጠው ደካማ አገልግሎት በህዝብ እያተወቀሰ ባለበት ጊዜ፣  አሁን ደግሞ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለመግባት ልዩ ፈቃድ መጠየቅ መጀመሩ፣ የድርጅቱን አገልገሎት የበለጠ የሚያወርደውና ከፍተኛ የንብረት ጉዳት እንዲደርስ የሚያደርግ ነው።